Website Survey

መሻር በዲሲ

Authored By: D.C. Bar Pro Bono Center

Information

ሕጋዊ ጋብቻ ማፍረስ አንድ ጋብቻ ዋጋ እንደሌለው በማረጋገጥ በፍርድ ቤት የሚሰጥ ፍርድ ነው። ሕጋዊ የጋብቻ ማፍረስ ውሳኔ ጋብቻውን ይሰረዘዋል - ሕጋዊ ውጤቱም ጋብቻው ከመጀመሪያውኑ እንዳልተፈጸመ የሚያስቆጥር ነው። ሃይማኖታዊ ጋብቻን ማፍረስ ከሕጋዊ ጋብቻን ማፍረስ የተለየ ነው። ስለ ሃይማኖታዊ ጋብቻ ማፍረስ በተመለከተ ተጨማሪ ለማወቅ ከፈለጉ የእርስዎን ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ያነጋግሩ። ሕጋዊ ጋብቻ ማፍረስ ከጋብቻ ፍቺም የተለየ ነው። የጋብቻ ፍቺ ተቀባይነት ያለውን የጋብቻ ውል እንዲያበቃ ያደርገዋል።

የእኔን ጋብቻ እንዲፈርስ ማድረግ እችላለሁ?

በዲሲ ውስጥ የጋብቻ ማፍረስ ድርጊቶች በጣም ብዙም ያልተለመዱ ናቸው። ጋብቻዎች ብዙውን ጊዜ በማይከሰቱ በጣም በተወሰኑ ሁኔታዎች ብቻ ሊፈርሱ ይችላሉ። በዲሲ ውስጥ ያለው ሕግ ፍርድ ቤቱ የእርስዎን ጋብቻ እንዲያፈርሰው በሚከተሉት ሁኔታዎች ብቻ እንዲጠይቁ ይፈቅድልዎታል፦

  • የእርስዎን የትዳር ጓደኛ ባገቡበት ጊዜ በአእምሮ ብቃት ምክንያት ከተጋቢዎች መካከል አንዳችሁ ለጋብቻው ፈቃደኝነታችሁን ለመግለጽ ብቁ ያልነበራችሁ እንደሆነ፤
  • በእርስዎ የትዳር ጓደኛ አስገዳጅነት ወይም የማጭበርበር ድርጊት ምክንያት የእርስዎን የትዳር ጓደኛ እንዲያገቡ ከተገደዱ፤
  • የእርስዎን የትዳር ጓደኛ ባገቡበት ጊዜ ዕድሜዎት ከ16 ዓመት በታች ከነበረ እና ዕድሜዎት 16 ዓመት ከሞላ በኋላ እንደ ባል እና ሚስት ሁለታችሁም በፈቃደኝነት መኖር ካልቀጠላችሁ፤
  • የእርስዎን የትዳር ጓደኛ ባገቡበት ጊዜ፣ ከሁለት አንዳችሁ ከሌላ ሰው ጋር ቀደም ሲል ተጋብታችሁ ከነበረ፤ ወይም
  • • የቅርብ ዘመድን ካገቡ።

ከነዚህ መስፈርቶች መካከል አንዱን ወይም ከዚያ በላይ እንደሚያሟሉ ፍርድ ቤቱ ካመነበት የእርስዎን ጋብቻ መፍረስን በማረጋገጥ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል።

የእኔን ጋብቻ እንዲፈርስ ለማድረግ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማግኘት አለብኝ?

ሕጋዊ (ሃይማኖታዊ ያልሆነ) የጋብቻ መፍረስን ማረጋገጫ ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ በሚከተሉት ምክንያቶች የጋብቻ መፍረስን የሚፈልጉ ከሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማግኘት አለብዎት፦

  • የእርስዎን የትዳር ጓደኛ ባገቡበት ጊዜ በአእምሮ ብቃት ምክንያት ከተጋቢዎች መካከል አንዳችሁ ለጋብቻው ፈቃደኝነታችሁን ለመግለጽ ብቁ ያልነበራችሁ እንደሆነ፤
  • በእርስዎ የትዳር ጓደኛ አስገዳጅነት ወይም የማጭበርበር ድርጊት ምክንያት የእርስዎን የትዳር ጓደኛ እንዲያገቡ ከተገደዱ፤
  • የእርስዎን የትዳር ጓደኛ ባገቡበት ጊዜ ዕድሜዎት ከ16 ዓመት በታች ነበረ እና ዕድሜዎት 16 ዓመት ከሞላ በኋላ እንደ ባል እና ሚስት ሁለታችሁም በፈቃደኝነት መኖር ካልቀጠላችሁ፤

እነዚህ ተቀባይነት የሌላቸው ጋብቻዎች ይባላሉ።

ሆኖም ግን አንዳንድ ጋብቻዎች ጋብቻው ከተፈጸመ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው (ይህም ማለት ተጋቢዎቹ ሰዎች ከመጀመሪያውኑ በሕጋዊ መንገድ በጭራሽ ያልተጋቡ ናቸው)። በዲሲ ያለው ሕግ ከዚህ በታች ያሉትን ዓይነት ጋብቻዎች ዕውቅና አይሰጣቸውም፦

  • በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ ወይም
  • ከዚህ ቀደም ተጋብተው የነበሩ እና ከዚህ ቀደም የነበረው ጋብቻቸው በሞት ወይም በፍርድ ቤት የፍቺ ትዕዛዝ ያልተቋረጠ ሰዎች መካከል የሚደረግ ጋብቻ (ይህም ማለት ከተጋቢዎቹ አንዱ አሁንም ድረስ ከሌላ ሰው ጋር የተጋባ ነው ማለት ነው)።

ከነዚህ ሁኔታዎች መካከል አንዳቸውም በእርስዎ ላይ ተፈጻሚነት ከሌላቸው፣ በሕጋዊ መንገድ በጭራሽ ያልተጋቡ ስለነበሩ የጋብቻ ማፍረሻ ወይም የፍቺ ትዕዛዝን ማግኘት አያስፈልግዎትም። ሆኖም ግን የእርስዎ ጋብቻ ተቀባይነት የሌለው እንደነበረ ግልጽ የሆነ ማስረጃን ለማግኘት አሁንም ድረስ የጋብቻ መፍረስ ትዕዛዝን ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባት ያስፈልግዎት ይሆናል።

በባሕላዊ መንገድ አግብቼ የነበርኩ ከሆነስ?

በሕጋዊ ሥነ ሥርዓት ወይም በባሕላዊ መንገድ ለተፈጸመ ለማናቸውም ዓይነት ጋብቻ የጋብቻ ማፍረሻ መስፈርቶቹ አንድ ዓይነት ናቸው።

የጋብቻ ማፍረስን ትዕዛዝ ለመጠየቅ ዲሲ ለእኔ ትክክለኛው ቦታ ነው?

በዲሲ ውስጥ ጋብቻ ፈጽመው የነበረ ከሆነ ወይም አሁን ላይ በዲሲ ውስጥ ሕጋዊ ነዋሪ ከሆኑ በዲሲ ውስጥ ጋብቻ እንዲፈርስልዎት መጠየቅ ይችላሉ።

ጋብቻ ማፍረስ ትዕዛዝን ማን ሊጠይቅ ይችላል?

ግለሰቡ ዕድሜው ስምምነቱን መግለጽ ከሚችልበት የተፈቀደ ዕድሜ በታች ከሆነ እና ግለሰቡ አሁንም ድረስ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ከሆነ (ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች ከሆነ) እና የጋብቻ ማፍረስ ትዕዛዝ ጥያቄ የሚቀርብ ከሆነ የአካለ መጠን ያልደረሰው ግለሰብ ወላጅ ወይም ሕጋዊ ሞግዚት ፍርድ ቤቱን በአካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ ፈንታ ጋብቻውን እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላል። ግለሰቡ በአእምሮ ብቃት ምክንያት ለጋብቻው ስምምነቱን መግለጽ እንደማይችል በዳኛ በተረጋገጠ ምክንያት የጋብቻ መፍረስ ጥያቄው እየቀረበ ያለ ከሆነ የዚያ ግለሰብ ሞግዚት ጋብቻው እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላል።

ለአካል መጠን ያልደረሰ ወይም የአእምሮ ብቃት የሌለው ሰው ካልሆነ በቀር “ጥያቄ ውስጥ የሚገባው” ሰው ጋብቻ እንዲፈርስ ጥያቄ ራሱ ማቅረብ አይችልም። ለምሳሌ የማጭበርበር ድርጊትን የፈጸመ ግለሰብ በራሱ ወይም በራሷ የማጭበርበር ድርጊት ለተፈጸመ ጋብቻ ለሚያቀርበው/ለምታቀርበው የጋብቻ ማፍርስ ጥያቄ ተቀባይነትን ሊያገኝ / ልታገኝ አይችልም/ አትችልም። በጥያቄ ውስጥ የሚገባው ሰው ጋብቻውን ማቋረጥ ከፈለገ እሱ ወይም እሷ የፍቺ ጥያቄን በአግባቡ ማቅረብ አለበት ወይም አለባት። በጥያቄ ውስጥ የማይገባው ግለሰብ ብቻ የጋብቻ መፍረስ የፍርድ ውሳኔን ሊያገኝ ይችላል።

የጋብቻ ማፍረስ ትዕዛዝን እንዴት መጠየቅ እችላለሁ?

ስለ የእርስዎ ጉዳይ ጠበቃን ሊያማክሩ ወይም የራስዎትን ጉዳይ ራስዎት ፋይል ሊያስገቡ ይችላሉ። አስፈላጊ የሆኑ የአቤቱታ አቀራረብ መረጃዎች (ሕጋዊ ሰነዶች) www.dcbar.org/pleadings ላይ ወይም በዲሲ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቤተሰብ ፍርድ ቤት መቀበያ ማእከል [D.C. Superior Court Family Court Central Intake Center (500 Indiana Avenue NW፣ ክፍል ቊጥር JM-540)] ከሰኞ እስከ ዓርብ ከጠዋቱ 8:30 a.m. እስከ 5:00 p.m. ማግኘት ይችላሉ።

የእኔ የትዳር ጓደኛ የጋብቻ መፍረስ ጥያቄን ቢያቀርብ እና እኔ ግን ባልስማማስ?

እርስዎ የማይስማሙበትን ምክንያቶች ለፍርድ ቤቱ በመንገር እና ፍርድ ቤቱን የጋብቻ መፍረስ ጥያቄውን እንዳያጸድቀው በመጠየቅ የመከራከሪያ ምላሽ የያዘ ፋይል ማስገባት ይችላሉ።

የጋብቻ መፍረስ ውሳኔ ሲሰጥ ምን ሌሎች ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ ሊመለከት ይችላል?

እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ ንብረት ወይም ልጆች በጋራ ካሉዋችሁ፣ እነዚህን ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ እንዲመለከታቸው ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ። እርስዎን እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ከደረሳችሁ ፍርድ ቤቱ የእናንተን ስምምነት የሚያንጸባርቅ ውሳኔን ሊሰጥ ይችላል። የማይስማሙ ከሆነ ችሎት ይቆምልዎታል እና በመቀጠል ዳኛው ውሳኔ ይሰጣል።

ቀለብ ማግኘት እችላለሁ?

የጋብቻው መፍረስ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ እርስዎ እየጠበቁ ሳለ ፍርድ ቤቱ ጊዜያዊ ቀለብን እንዲሰፈርልዎት ሊያዝ ይችላል ሆኖም ግን የጋብቻ መፍረሱ ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ከሆነ በኋላ ግን ቀለብ ሊሰፈርልዎት አይችልም። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፣ “በዲሲ ውስጥ ቀለብ አሰፋፈር” የሚለውን መረጃ ሰጪ ሰነድ ይመልከቱ።

የጋብቻ መፍረስ ውሳኔ የመጨረሻ የሚሆነው መቼ ነው?

ከችሎቱ በኋላ ዳኛው የጋብቻ መፍረስ ውሳኔን ከሰጡ የትዕዛዙ ቅጂ ይሰጥዎታል። የእርስዎ የጋብቻ መፍረስ ውሳኔ ከችሎቱ ጥቂት ቀናት በኋላ ሊሆን በሚችለው “ከችሎቱ መመዝገቢያ ቀን” በኋላ ካሉት 30 ቀናት በኋላ የመጨረሻ ይሆናል። ከተከራካሪ ወገኖች መካከል አንዳቸው በነዚያ 30 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ሊጠይቁ እና የጋብቻ መፍረስ ትዕዛዙን እንዲያቆየው (ይህም ማለት የመጨረሻ ውሳኔ እንደሆነ ሳያደርግ እንዲይዘው) ለመጠየቅ ይችላሉ። ማቆየት ውሳኔ ከተሰጠ፣ ትዕዛዙ የይግባኝ ጥያቄው መፍትሔ ሲሰጥበት የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል። የማቆየት ውሳኔው ውድቅ ከተደረገ ትዕዛዙ ከ30 ቀናቱ በኋላ አሁንም ድረስ የመጨረሻ ውሳኔ መሆኑን ይቀጥላል። የዳኛውን ውሳኔ ይግባኝ ልትጠይቁበት እንደማትፈልጉ ሁለታችሁም ከተስማማችሁ፣ የጋራ የይግባኝ ጥያቄ ይለፈኝ [Joint Waiver of Appeal] ልታስገቡ እና የ30-ቀን የመቆያ ጊዜው አይኖርም እንዲሁም ትዕዛዙ ወዲያውኑ የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል።

ለተጨማሪ መረጃ፣

ያለ ቀጠሮ ነጻ የምክር አገልግሎት የሚሰጠውን የቤተሰብ ፍርድ ቤት ራስ-አገዝ ማእከል [Family Court Self- Help Center] የሚባለውን በ DC Superior Court, 500 Indiana Avenue, NW ውስጥ በክፍል ቊጥር JM-570 ላይ ሊጎበኙት ይችላሉ። ማእከሉ ከሰኞ እስከ ዓርብ ከጠዋቱ 8:00 a.m. እስከ 5:30 p.m. ድረስ ክፍት ነው። ማእከሉ የፍርድ ሂደቱን ለእርስዎ ሊያብራራልዎት፣ ተገቢነት ያላቸውን ሕጋዊ ወረቀቶች በመሙላት ላይ እርስዎን ሊያግዝዎት፣ እና ወደ ሌላ ነጻ የሕግ አገልግሎት ሰጪዎች ሊመራዎት ይችላል። ለተጨማሪ መረጃ እና እንዴት ነጻ የሕግ አገልግሎት ድርጅቶችን ማነጋገር እንደሚቻል ለማወቅ www.lawhelp.org/dc ይጎብኙ ወይም ስለነዚህ ነገሮች የተቀረጹ መልእክቶችን ለማዳመጥ ወደ D.C. Bar Legal Information Helpline በስልክ ቊጥር 202-626-3499 ይደውሉ።

የ D.C. Bar Pro Bono Center አጠቃላይ መረጃን ብቻ ይሰጣል። ይህ ሕጋዊ የምክር አገልግሎት አይደለም። ሕጋዊ የምክር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት ከጠበቃ ብቻ ነው። ለአንድ የተወሰነ ሁኔታ ሕጋዊ የምክር አገልግሎት ከፈለጉ፣ ጠበቃ ያነጋግሩ። ሕጋዊ ትምህርት ሰጪ ማቴሪያሎችን ወቅታቸውን የጠበቁ ለማድረግ እንሞክራለን፣ ሆኖም ግን ሕጎች በፍጥነት ደጋግመው ይቀያየራሉ። በመሆኑም የ D.C. Bar Pro Bono Center የሚሰጠውን መረጃ ትክክለኛነት ዋስትና ሊሰጥ አይችልም

This resource has been translated into Spanish, French, and Amharic thanks to the American Bar Endowment.
Last Review and Update: Oct 01, 2018
Back to top