Website Survey

ፍቺ በዲ.ሲ

Authored By: D.C. Bar Pro Bono Center

Information

ፍቺ ጋብቻን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሕጋዊ መንገድ ነው። የፍቺ ሰነዶችን በማስገባት የፍቺ የፍርድ ቤት ክስ ሂደቱን የሚያስጀምረው የትዳር ጓደኛ ከሳሽ፣ በመባል ሲታወቅ ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ተከሳሽ በመባል ይታወቃል። የፍቺ ጥያቄ ተቃውሞ ሊቀርብበት ወይም ተቃውሞ ላይቀብበት ይችላል።

በዲሲ ውስጥ የጋብቻ ጥያቄን ማቅረብ እችላለሁ?

በዲሲ ውስጥ ጋብቻ ለመፈጸም ብቁ ለመሆን የሚከተሉትን ሦስት መስፈርቶች ማሟላት አለብዎት፦ የነዋሪነት ፈቃድ፣ የጋብቻ ማረጋገጫ እና የፍቺ ምክንያቶች።

የነዋሪነት መስፈርቱን ለማሟላት፣ እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ እርስዎ ለፍጹም ፍቺ አቤቱታ በሚያቀርቡበት ጊዜ ቢያንስ ለስድስት ወራት ያለማቋረጥ በዲሲ ውስጥ የኖራችሁ መሆን አለባችሁ።

የመስፈርቱን የጋብቻ ማረጋገጫ ለማሟላት፣ ከሳሹ ፍርድ ቤቱ የፍቺ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ሕጋዊነት ያለው ጋብቻ ስለመኖሩ ማረጋገጫ ማቅረብ መቻል አለበት። ከሳሹ የጋብቻ ምስክር ወረቀቱን ኦፊሴላዊ ቅጂ፦ ፎቶኮፒውን ሳይሆን ኦርጂናሉን ወይም የተረጋገጨ ቅጂ ይዞ መቅረብ አለበት። እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ በዲሲ ውስጥ ከሆነ የተጋባችሁት የጋብቻ ምስክር ወረቀቱን ከ Marriage Bureau፣ D.C. Superior Court, 500 Indiana Avenue, NW፣ ክፍል ቊጥር JM-690 ማግኘት ይችላሉ። የባሕል ጋብቻ የፈጸማችሁ እና ምንም ዓይነት የጋብቻ ምስክር ወረቀት ከሌላችሁ፣ ከሳሹ የባሕል ጋብቻ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ በጓደኞች እና ቤተሰብ አባላት ቃለ መሐላ ወይም በአስረጂ ሰነዶች አማካኝነት ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል።

የፍቺ ምክንያቶችን መስፈርት ለማሟላት እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ ለተወሰነ ጊዜ ተለያይታችሁ የነበራችሁ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብዎታል። ዲሲ ምንም እንከንን የማያስተናገድ ፍርድ ቤት ክልል ነው፤ ይህም ማለት ጋብቻን ለመፈጸም ሁለት ዓይነት ምክንያቶች ብቻ ተቀባይነት አላቸው፦

  1. ለስድስት ወራት የዘላቀ በጋራ ስምምነት የተፈጸመ መለያየት፦ እርስዎ የፍቻ ጥያቄ ከማቅረብዎ በፊት እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ በአንድ ላይ እና በፈቃደኝት ለመለያየት ወስናችሁ ለየብቻችሁ ስትኖሩ የቆያችሁ፣ ምንም ዓይነት ንክኪ (ወሲባዊ ግንኙነት ሳይኖራችሁ) ቢያንስ ለስድስት ወራት የቆያችሁ መሆን አለባችሁ፤
  2. ለአንድ ዓመት የቆየ መለያየት፦ እርስዎ ለመለያየት ቢስማሙም ባይስማሙም፣ እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ ለየብቻ እና ተነጣጥላችሁ በተለያየ ቦታ፣ ያለምንም ዓይነት ንክኪ (ወሲባዊ ግንኙነት ሳይኖችሁ) ቢያንስ ለአንድ ዓመት የቆያችሁ መሆን አለባችሁ።

ምንም እንኳ እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ በአንድ ተመሳሳይ ቤት ወይም አፓርታማ ውስጥ የምትኖሩ ቢሆንም ተለያይታችሁ እና ተነጣጥላችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁ። ሆኖም ግን የተለያየ ሕይወት እየኖራችሁ ስለመቆየታችሁ “አልጋም ሆነ ጊዜ” እንዳልተጋራችሁ ለፍርድ ቤቱ ማሳመን መቻለ አለባችሁ። ይህ ማለት ሁለታችሁም የተለያየ መኝታ ቤት ነበራችሁ፣ አንድ ላይ እንደ ጥንዶች አልወጣችሁም፣ ምግብ አብራችሁ አልበላችሁም፣ ክፍያ መጠየቂያዎችን አንድ ላይ አልከፈላችሁም ወይም በማናቸውም ሌላ መልኩ እንደ ተጋቢ ባልና ሚስት ምንም ዓይነት ድርጊት በጋራ አልፈጸማችሁም ማለት ነው።

ሕጋዊ ፍቺ ምን ማለት ነው? በዲሲ ውስጥ ለመፋታት ሕጋዊ ፍቺ ማግኘት ያስፈልገኛል?

በዲሲ ውስጥ ፍቺን ለማስመዘገብ ሕጋዊ ፍቺ እንዲኖርዎት አይገደዱም። ሕጋዊ ፍቺ ማለት የተለያዩ የትዳር ጓደኞች በፍርድ ቤት የጸደቀ ፍቺ ሳይኖራቸው የልጅ አያያዝ፣ የልጅ ቀለብ እና የንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ከፍርድ ቤት የሚያገኙት ትዕዛዝ ነው። ምንም እንኳ የትዳር ጓደኞቹ ለየብቻ እና ተለያይተው የሚኖሩ ቢሆኑም እነዚህ ሕጋዊ ጉዳዮች መፍትሔ ያገኙ ቢሆኑም በዚህ ሁኔታ እንደተጋባችሁ ትቀጥላላችሁ እና ዳግመኛ ሌላ ሰው ለማግባት ነጻ አይደላችሁም።

እኔ ከሳሽ ወይም ተከሳሽ መሆኔ የሚያሰከትለው ለውጥ ወይም ተጽዕኖ ይኖር ይሆን?

በአብዛኛው ሁኔታ ላይ አይኖርም። በፍቺ ሁኔታ ላይ ዋንኛው ለውጥ የፍቺ ጥያቄው ክርክር የማይደረግበት ከሆነ ከሳሽ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እና ለአጭር ጊዜ በሚቆም ችሎት ላይ የምስክርነት ቃሉን መስጠት የሚኖርበት ሲሆን ተከሳሽ ደግሞ በፍርድ ቤት መቅረብ ላያስፈልገው ይችል ይሆናል። የጋብቻ ፍቺ ጥያቄው ክርክር የሚደረግበት ከሆነ እና ተከራካሪ ወገኖች ከስምምነት ላይ ካልደረሱ ሁለቱም ወገኖች መገኘት የሚኖርባቸው የፍርድ ክርክር ሂደት ይኖራል። በፍርድ ቤት ክርክር ጊዜ ከሳሽ ማስረጃውን ወይም ማስረጃዋን በመጀመሪያ ያቀርባል ወይም ታቀርባለች።

ክርክር በሚደረግበት እና ክርክር በማይደረግበት ፍቺ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ ለመፋታት እና በጋብቻ ላይ እያላችሁ ያፈራችሁትን ንብረት (እሴቶችን እና ዕዳዎችን ይጨምራል)፣ የልጅ አያያዝን እና ቀለብን መጋራት፣ እንዲሁም አንዱ ወገን ለሌላው ቀለብ መቁረጥ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት ሙሉ በሙሉ ከተስማማችሁ ፍቺው ክርክር የማይደረግበት ፍቺ ነው። እርስዎ እና የእርስዎ የትዳር ጓደኛ በነዚህ ጉዳዮች ላይ በማናቸውም ላይ ከስምምነት ላይ ሳትደርሱ ብትቀሩ እና ፍርድ ቤት እንዲወስናላችሁ የምትጠይቁ ከሆነ ምንም እንኳ ሁለታችሁም ፍቺው እንዲጸድቅላችሁ የተስማማችሁ ቢሆንም ፍቺው ክርክር የሚደረግበት ይሆናል። መረጃ መስጫ ወረቀቶችን ለማንበብ የሚፈልጉ ከሆነ ዓባሪ የተያያዙትን “በዲሲ ውስጥ የልጅ ድጋፍ”፣ “በዲሲ ውስጥ የቀለብ አከፋፈል” እና “የልጅ አያያዝ በዲሲ ውስጥ” የሚሉትን ማንበብ ይችላሉ።

አሁን ፍቺ ፍርድ ማግኘት እና ሌላውን ነገር በሙሉ ቀስ ብዬ በኋላ ላይ ማስተካከል እችላለሁ?

እንደሁኔታው ይወሰናል። የእርስዎ ፍቺ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ነው፣ ወደ ፍርድ ቤት መመለስ እና ዳኛውን ቀለብን በተመለከተ ወይም በጋብቻ ላይ ስላፈራችሁት ንብረት ክፍፍል ውሳኔ እንዲሰጡልዎት ጥያቄ ማቅረብ አይችሉም፤ እንዲህ ያሉት ነገሮች መፍትሔ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ ከሆነ ፍቺው በሚፈጸምበት ጊዜ ሊያቀርቧቸው ይገባዎታል። ሆኖም ግን በኋላ ላይ ወደ ፍርድ ቤቱ ተመልሰው በመሄድ የልጅ አያያዝ ወይም የልጅ ድጋፍ ትዕዛዝን እንዲሰጡልዎት መጠየቅ ይችላሉ። ዲሲ ለልጅ አያያዝ ወይም ለልጅ የድጋፍ ጥያቄ ማመልከቻ ለማስገባት ለእርስዎ ትክክለኛው ቦታ ነው ብለው ካሰቡ፣ “ልጅ አያያዝ እና የልጅ ድጋፍ” የሚል ርዕስ ያለውን መረጃ ሰጪ ወረቀት ያንብቡ።

በጋብቻ የፈራ ንብረት ምንድን ነው?

በጋብቻ የፈራ ንብረት በጋብቻ ወቅት የተገኙ እሴቶችን እና ዕዳዎችን ያካትታል። እሴቶች መኖሪያ ቤቶችን እና ሌሎች ሪል እስቴትን፣ ገንዘብ (የባንክ ሒሳቦች)፣ የግል ንብረት (እንደ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ወይም መኪናዎች) እና የጡረታ መድን ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞችን ያካትታል። ዕዳዎች ብድሮች፣ የክሬዲት ካርድ ዕዳ እና ታክሶችን ሊያካትቱ ይችላሉ። በዲሲ ውስጥ በንብረቱ ባለቤትነት ላይ ወይም በዕዳው ላይ የማን ስም እንደተጠቀሰ ምንም ትርጉም አይሰጥም ወይም በተመሳሳይ መልኩ አንዱ ብቻ የትዳር ጓደኛ ለንብረቱ ቢከፍልም ሌላኛው እንዳልከፈለ ተደርጎ አይቆጠርም።

ንጥል የራስ ንብረት አንዱ የትዳር ጓደኛ ከጋብቻው በፊት በባለቤትነት የያዘው እና በጋብቻው ጊዜ በሙሉ እንደ የግል ንብረቱ አድርጎ በተናጠል የያዘው ንብረት ነው። ንጥል የራስ ንብረት በተጨማሪ ለአንዱ ተጋቢ የትዳር ጓደኛ ብቻ በጋብቻ ወቅት የተሰጡ ማናቸውም ስጦታዎች ወይም ውርሶችን ሊያካትት ይችላል።

የትኛው ንብረት በጋብቻ የፈራ እና ማን ምን እንደሚያገኝ እኔ እና ባለቤቴ ከስምምነት ላይ ሳንደርስ ብንቀርስ?

ከሁለት አንዳችሁ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥላችሁ ከጠየቃችሁ፣ ዳኛው የትኛው ንብረት በጋብቻ የፈራ ንብረት እንደሆነ እና በጋብቻ የፈራው ንብረት “ፍትሐዊ በሆነ እና በርትዓዊ መንገድ” ለማን እንደሚገባ በማከፋፈል ውሳኔ ይሰጣል። በጋብቻ የፈራው ንብረትን በማከፋፈል ሂደት ላይ “ሁሉንም ተዛማጅነት ያላቸውን ሁኔታዎች” ከግምግ እንዲያስገባ ሕጉ ዳኛውን ያስገድደዋል።

የእኔን ስም መለወጥ ብፈልግስ?

ከሁለቱ ወገኖች አንዱ ወደ ቀድሞ የነበረ ስሙ እየተመለሰ ያለ እስከሆነ ድረስ እና ይህንንም የሚያደርገው ለማጭበርበር ዓላማ እስካልሆነ ድረስ (ለምሳሌ በዕዳ ከመጠየቅ ለመዳን እስካልሆነ ድረስ) የስም ለውጥን ለማድረግ ሁለቱም ባለትዳሮች ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ።

ክርክር የማይደረግበት የፍቺ ውሳኔን እንዴት እንዲጀምር ማድረግ እችላለሁ?

ክርክር የማይደረግበት የፍቺ ውሳኔ ክርክር ከሚደረግበት የፍቺ ውሳኔ ይልቅ በፍርድ ቤት ሥርዓት ውስጥ በፍጥነት ይስተናገዳል። እርስዎ እና የትዳር ጓደኛዎ ለፍጹም ፍቺ አቤቱታ እና የፍቃድ ምላሽ በተመሳሳይ ጊዜ ፋይል ማስገባት ትችላላችሁ እና ከሳሹ ለተከሳሽ ወረቀቶቹን አስቀድሞ መስጠት አይገደድም። “ክርክር የማይደረግባቸው ፍቺዎች በዲሲ ውስጥ” የሚለውን መረጃ ሰጪ ወረቀት ይመልከቱ።

ክርክር የሚደረግበትን ፍቺ ውሳኔን እንዴት መጀመር እችላለሁ?

ክርክሩን የሚያስጀምሩት እርስዎ ከሆኑ እርስዎ ከሳሽ ነዎት። የፍጹም ፍቺ አቤቱታን ማስገባት አለብዎት። መጥሪያ፣ የወሳኝ ኹነቶች ቅጽ እና የቤተሰብ ፍርድ ቤት ተሻጋጋሪ ዋቢ ቅጽን በተጨማሪ መሙላት ይኖርብዎታል። አቤቱታውን ፋይል ሲያስገቡ የመጀመሪያው የፍርድ ቤት ችሎት የሚቆምበት (መነሻ ችሎት የሚቆምበት ቀን) ቀነ ቀጠሮ ይቆረጣል። ይህ መአጃ ለእርስዎ ይሰጥዎታል እና ለእርስዎ የትዳር ጓደኛ በሚሰጡት ወረቀቶች ላይ መካተት አለበት። አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ በጣም ውስን በሆኑ የሕግ መስፈርቶች መሠረት ለእርስዎ የትዳር ጓደኛ ሁሉንም ወረቀቶች መስጠት ወይም እንዲደርሳቸው ማድረግ ይኖርብዎታል።

“በዲስ ውስጥ የፍርድ ቤት ወረቀቶች አሰጣጥ” የሚለውን መረጃ ሰጪ ወረቀት ይመልከቱ። ለሌላኛው ወገን እንዴት የፍርድ ቤት ወረቀቶች እንደሚሰጡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ፍቺ እና የልጅ አያያዝ የፍርድ ቤት ክርክሮች” የሚለውን ይመልከቱ።

ክርክሩን ያስጀምሩት የእርስዎ ባለቤት ከሆኑ እርስዎ ተከሳሽ ነዎት። የአቤቱታ ሰነድ ቅጂ በሕጋዊ መንገድ ከተሰጥዎት በኋላ የእርስዎ ምላሽ በ20 ቀናት ውስጥ ማስገባት አለብዎት። የእርስዎን ምላሽ ካስገቡ በኋላ ለእርስዎ የትዳር ጓደኛ ቅጂውን ሊሰጡ ይገባዎታል።

የእርስዎ ጉዳይ ምንም እንኳ ክርክር የሚደረግበት ቢሆንም ያለ ፍርድ ቤት ክርክር ሊፈቱት ይችሉ ይሆናል። የቤተሰብ ፍርድ ቤት [Family Court] ከእርስዎና ከእርስዎ የትዳር ጓደኛ ጋር በእናንተ የፍቺ ሁኔታ ላይ መደራደር እንድትችሉ የሠለጠነ የግልግል ዳኝነት አገልግሎትን በሚሰጠው በብዝሐ በር ያለመግባባትን መፍትሔ ሰጪ ዲቪዝዮን [Multi-Door Dispute Resolution Division (202-879-1549)] በኩል የግልግል ዳኝነት አገልግሎትን በነጻ ይሰጣል።

ፍቺ ውሳኔ የመጨረሻ የሚሆነው መቼ ነው?

ዳኛው የፍቺ ውሳኔ ከሰጠ ከችሎቱ በኋላ ወዲያውኑ ወይም በፖስታ ቤት በኩል የፍቺ ውሳኔውን ትዕዛዝ ቅጂ ያገኛሉ። ከእርስዎ ችሎት በኋላ ጥቂት ቀናትን ሊወስድ በሚችለው በፍርድ ቤቱ እንደ “በችሎት ላይ ቀርቧል” የሚል ማኅተም ከተመታበት ቀን ጀምሮ ካሉት 30 ቀናት በኋላ የእርስዎ ፍቺ ትዕዛዝ የመጨረሻው ውሳኔ ይሆናል። ከተከራካሪ ወገኖች አንዳቸው በነዚያ 30 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ፋይል ሊያስገቡ እና ፍርድ ቤቱ የፍቺ ትዕዛዙን እንዲያቆየው (ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፈው) መጠየቅ ይችላሉ። ማቆየት ውሳኔ ከተሰጠ፣ ትዕዛዙ የይግባኝ ጥያቄው መፍትሔ እስኪሰጥበት ድረስ የመጨረሻ ውሳኔ አይሆንም። የእርስዎ የማቆየት ጥያቄ ከተከለከለ፣ ትዕዛዙ ይግባኙ እየታየ እያለ ትዕዛዙ ተፈጻሚ እንደሆነ ይቀጥላል። የዳኛውን ውሳኔ ይግባኝ ልትጠይቁበት እንደማትፈልጉ ሁለታችሁም ከተስማማችሁ፣ የጋራ የይግባኝ ጥያቄ ይለፈኝ [Joint Waiver of Appeal] ልታስገቡ እና የ30-ቀን የመቆያ ጊዜው አይኖርም እንዲሁም ትዕዛዙ ወዲያውኑ የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል።

አስፈላጊ የሆኑ የአቤቱታ አቀራረብ መረጃዎች (ሕጋዊ ሰነዶች) www.dcbar.org/pleadings ላይ ወይም በዲሲ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቤተሰብ ፍርድ ቤት መቀበያ ማእከል [D.C. Superior Court Family Court Central Intake Center (ክፍል ቊጥር JM-540) ከሰኞ እስከ ዓርብ ከጠዋቱ 8:30 a.m. እስከ 5:00 p.m. ማግኘት ይችላሉ።

ለተጨማሪ መረጃ፣

ያለ ቀጠሮ ነጻ የምክር አገልግሎት የሚሰጠውን የቤተሰብ ፍርድ ቤት ራስ-አገዝ ማእከል [Family Court Self- Help Center] የሚባለውን በ DC Superior Court, 500 Indiana Avenue, NW ውስጥ በክፍል ቊጥር JM-570 ላይ ሊጎበኙት ይችላሉ። ማእከሉ ከሰኞ እስከ ዓርብ ከጠዋቱ 8:00 a.m. እስከ 5:30 p.m. ድረስ ክፍት ነው። ማእከሉ የፍርድ ሂደቱን ለእርስዎ ሊያብራራልዎት፣ ተገቢነት ያላቸውን ሕጋዊ ወረቀቶች በመሙላት ላይ እርስዎን ሊያግዝዎት፣ እና ወደ ሌላ ነጻ የሕግ አገልግሎት ሰጪዎች ሊመራዎት ይችላል። ለተጨማሪ መረጃ እና እንዴት ነጻ የሕግ አገልግሎት ሰጪዎችን ማነጋገር እንደሚቻል ለማወቅ www.lawhelp.org/dc ይጎብኙ ወይም ስለነዚህ ነገሮች የተቀረጹ መልእክቶችን ለማዳመጥ ወደ D.C. Bar Legal Information Helpline በስልክ ቊጥር 202-626-3499 ይደውሉ።

የ D.C. Bar Pro Bono Center አጠቃላይ መረጃን ብቻ ይሰጣል። ይህ ሕጋዊ የምክር አገልግሎት አይደለም። ሕጋዊ የምክር አገልግሎት ማግኘት የሚችሉት ከጠበቃ ብቻ ነው። ለአንድ የተወሰነ ሁኔታ ሕጋዊ የምክር አገልግሎት ከፈለጉ፣ ጠበቃ ያነጋግሩ። ሕጋዊ ትምህርት ሰጪ ማቴሪያሎችን ወቅታቸውን የጠበቁ ለማድረግ እንሞክራለን፣ ሆኖም ግን ሕጎች በፍጥነት ደጋግመው ይቀያየራሉ። በመሆኑም የ D.C. Bar Pro Bono Center የሚሰጠውን መረጃ ትክክለኛነት ዋስትና ሊሰጥ አይችልም

This resource has been translated into Spanish, French, and Amharic thanks to the American Bar Endowment.
Last Review and Update: Feb 14, 2024
Back to top