Website Survey

እርስዎ በ ICE ከታሰሩ የእርስዎን የወላጅነት መብቶች እንዴት ማስከበር እንደሚችሉ

Information

ይህ መመሪያ ጽሑፍ ሊጠቅማቸው ለሚችሉ ማናቸውም ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ለማሠራጨት እባክዎ ነጻነት ይሰማዎት።

አዘጋጆች ስቴፕቶ ኤንድ ጆንሰን የሕግ ባለሙያዎች [Steptoe & Johnson LLP]፣ ወሳኝ ለሆነው ትልቅ እገዛቸው ከፍተኛ ምስጋና ለአዩዳ [AYUDA]፣ የሕፃናት ሕግ ማእከል [Children's Law Center]፣ እና ለካፒታል አካባቢ የስደተኛ መብቶች ቅንጅት [Capital Area Immigrant Rights Coalition] ይድረሳቸው።

ሊንድሴይ ማርሻል [Lindsay Marshall]፣ ሎረን ዳሴ [Lauren Dasse]፣ ሎሪ ሜሩድ [Laurie Melrood] እና ሲንዲ ሽሎሰር [Cindy Schlosser] "በአሪዞና ውስጥ በ ICE ብታሰርስ” የሚለውን በማዘጋጀት ላይ ሁሉም በጣም አስፈላጊ ነበሩና ትልቅ ምስጋናችን ይድረሳቸው። የስፓኒሽኛ ቋንቋ ትርጉምን በማዘጋጀት ላይ ግሎባል ኮሙዩኒቲ ኢን አክሽን [Global Community in Action] ላደረጉት እገዛ እናመሰግናቸዋለን።

© 2017 - Steptoe & Johnson LLP

ይህ መመሪያ ጽሑፍ ሕጋዊ ምክር አገልግሎትን አይሰጥም እንዲሁም ይህን መመሪያ ጽሑፍ ስለተጠቀሙ ብቻ ከስቴፕቶ ኤንድ ጆንሰን የሕግ ባለሙያዎች [Steptoe & Johnson LLP]፣ ከአዩዳ [Ayuda]፣ ከየሕፃናት የሕግ ማእከል [Children’s Law Center]፣

ወይም ከካፒታል አካባቢ የስደተኛ መብቶች ቅንጅት [Capital Area Immigrant Rights Coalition] ጋር ምንም ዓይነት የጠበቃና ደንበኛ ግንኙነትን እንደተፈጠረ ተደርጎ አያስቆጥርም።

This is the first of a two-part guide. You can find the second part here and download the entire guide here.

የዚህ መመሪያ ጽሑፍ ዓላማ

በኮሎምቢያ ዲስትሪክት የሚኖሩ ስደተኛ ወላጅ ከሆኑ፣ ይህ መመሪያ ጽሑፍ የተጻፈው ለእርስዎ ነው። ዓላማው የኢሚግሬሽን እና የሕፃን ደኅንነት ጥበቃ ሥርዓቶቹን በተመለከተ ለእርስዎ ግንዛቤ ለመስጠት እና በኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ ሕግ አስከባሪ አካል [Immigration and Customs Enforcement (ICE)] በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በልጆችዎ ላይ ያልዎትን መብት እንዳያጡ ዕቅድ ማዘጋጀት እንዲችሉ እርስዎን ለማገዝ የታለመ ነው። የእርስዎ ቤተሰብ አንድ ላይ መቆየት መቻሉን እርግጠኛ ለመሆን እንዲችሉ ማድረግ የሚችሉት ከሁሉም የተሻለ ነገር መረጃ እንዲኖርዎት ማድረግ እና ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ነው!

ይህ መመሪያ ጽሑፍ ይህን እንዲያደርጉ እርስዎን ለማገዝ ተብሎ የተዘጋጀ ነው። በበጎ ፈቃደኛ ጠበቆች፣ የመብት ተከራካሪዎች፣ እና የቤተሰብ ሕግ እና የኢሚግሬሽን ኤክስፐርቶች አነስተኛ የቡድን ስብስብ አማካኝነት የተዘጋጀ ነው። በአጠቃላይ አነጋገር፣ በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ላይ የተብራራውን ዕቅድ አወጣጥ ለመከተል ጠበቃ መቅጠር አያስፈልግዎትም። ሆኖም ግን በተለይ የሕፃን እና የቤተሰብ አገልግሎቶች ኤጀንሲ [Child and Family Services Agency (CFSA)] የተባለው የዲሲ የሕፃን ጥበቃ ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም በእርስዎ ቤተሰብ ጉዳይ ላይ እጁ ገብቶበት ከነበረ ወይም በሠሩት ጥፋት ምክንያት ታስረው፣ ተከሰው ወይም ተፈርዶብዎት የሚያውቁ ከሆነ እርስዎ በግልዎ ያልዎትን የተሻሉ አማራጮች ይበልጥ መረዳት እንዲችሉ በዚህ ረገድ ልምድ ያለው የኢሚግሬሽን ጠበቃ እና የቤተሰብ ሕግ ነገረ ፈጅ እንዲያማክሩ እንመክርዎታለን። የኢሚግሬሽን እገዛ የሚሰጡ እና የቤተሰብ ሕግ ላይ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችን በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ክፍል 3 ላይ በአካባቢዎ የሚገኙ የሕግ ምክር አገልግሎቶች ሰጪ ድርጅቶችን ዝርዝር ማግኘት ይችላሉ። በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ላይ የቀረበው መረጃ ሥርዓቱን መረዳት እንዲችሉ እና ለእርስዎ ቤተሰብ ዕቅድ ማውጣት እንዲችሉ እርስዎን ለማገዝ ተብሎ የተዘጋጀ ነው ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ሕጋዊ ምክርን አይሰጥም።

በቁጥጥር ሥር መዋል

እኔ በ ICE ታስሬያለሁ፣ እና ምን ማድረግ አለብኝ?

አብዛኛዎቹ ሰዎች በ ICE ድንገት ሳይታሰብ በቁጥጥር ሥር ይውላሉ። የ ICE መኮንን ዝም ብሎ ድንገት ወደ ቤትዎ ወይም ወደ ሥራ ቦታዎ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሊመጣ ይችላል። ለ ICE ልጆች እንዳልዎት፣ መታሰር እንደማይፈልጉ፣ ከተለቀቁ ከእርስዎ የሚፈለግብዎትን ሁሉ አሟልተው እንደሚቀርቡና ለሚሰጥዎት ትዕዛዝ ተገዢ እንደሚሆኑ ይንገሩዋችው እና ከልጆችዎ እንዳይነጥልዎት ይለምኑዋቸው። ካሰርዎት፣ ለሁሉም እርስዎን የሚያገኝዎት የ ICE መኮንንን ይህንኑ መንገርዎትን ይቀጥሉ።

ICE በመጀመሪያ ሲመጣ የእርስዎ ልጆች ከእርስዎ ጋር ከነበሩ፣ ወዲያውኑ ስልክ መደወል እንዳለብዎት ለመኮንኖቹ ለማሳመን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት ማለት ነው፤ ልጆችዎ ብቻቸውን እንዳይቀሩ እና በሕፃን እና ቤተሰብ አገልግሎት ኤጀንሲ [Child and Family Service Agency (CFSA)] እንዳይወሰዱ ለማድረግ ለሆነ ለሌላ ሰው ስልክ መደወል እንዳለብዎት ለመኮንኖቹ መንገር ይኖርብዎታል።

እርስዎ በ ICE በሚያዙበት ጊዜ የእርስዎ ልጆች ከእርስዎ ጋር በአጠገብዎ የሌሉ ከሆነ እርስዎ ልጆች እንዳልዎት እና ቢለቅዎት በሚሰጥዎት ትዕዛዝ ተገዢ እንደሚሆኑ ለ ICE ሹም ይንገሩት እንዲሁም ከልጆችዎ እንዳይነጥልዎት መኮንኑን ይለምኑዋቸው። ካሰርዎት፣ ለሁሉም እርስዎን የሚያገኝዎት የ ICE መኮንንን ይህንኑ ያብራሩ።

ICE ለእርስዎ ክብካቤ ሰጪ ወይም የድንገተኛ አደጋ ተጠሪ እንደተያዙ ትንሽ ቆየት ብሎ ወዲያውኑ ስልክ እንዲደውሉ መፍቀድ አለበት፤ እንዲህ በመደረጉም ስልክ ለሚደውሉላቸው ሰው መታሰርዎትን መንገር ይችላሉ እነርሱም ለልጆችዎ እርስዎ ባዘጋጁት የድንገተኛ ሁኔታ ዕቅዶች መሠረት መመራት ይኖርባቸዋል። በደኅንነት ጥንቃቄ ምክንያት ስልክ መደወል እንደማይችሉ ከተነገርዎት የእርስዎ ልጆች በ CFSA እንዳይወሰዱ ለእርስዎ ልጆች ያዘጋጁት ዕቅድ ተፈጻሚ እንዲሆን ስልክ መደወል እንዳለብዎት ደጋግመው መናገርዎትን እርግጠኛ ይሁኑ።

ቊጥር ["A Number"] ምንድን ነው?

እርስዎ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ፣ ICE እርስዎን የውጭ ዜጋ ምዝገባ ቊጥር ወይም A Number ይሰጥዎታል (ከዚህ ቀደም የተሰጥዎት ከሆነ ያልዎትን የእርስዎን ነባር A number ይጠቀማል)። ይህ የእርስዎ የኢሚግሬሽን ጉዳይ መለያ ቊጥር ሲሆን በሁሉም የእርስዎ የኢሚግሬሽን ሂደት ላይ እርስዎን ይከተልዎታል። ይህን ቊጥር በወረቀት ጽፎ መያዝ እና ለእርስዎ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ፣ ዘመዶች፣ እና የቅርብ ጓደኞች - በስልክ ወይም ለእነርሱ ደብዳቤ በመጻፍ ይስጧቸው። በአጠቃላይ አነጋገር፣ የእርስዎ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ እና ሌሎች እርስዎ የት እንደታሰሩ እና ስለ የእርስዎ ጉዳይ መረጃ ማግኘት የሚችሉት የእርስዎ A Number ካላቸው ብቻ ነው።

ካልተፈታሁ እና የእኔን ልጆች ማንም ሄዶ ካልያዛቸው ምን ሊፈጠር ይችላል?

እርስዎ በ ICE በሚያዙበት ጊዜ ለእርስዎ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ ሆነ ወይም ወዲያውኑ የእርስዎን ልጆች ሊይዝልዎት ፈቃደኛ የሆነ እና ሊይዝ የሚችል ሌላ የታመነ ዘመድ ወይም ጓደኛ ማሳወቅ ሳይችሉ ከቀሩ የሕፃን እና ቤተሰብ አገልግሎቶች ኤጀንሲ [Child and Family Services Agency (CFSA)] የእርስዎን ልጆች ይወስዳቸዋል። ሆኖም ግን፣ የእርስዎ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ CFSA ን ካነጋገረ እና የልጅ ሞግዚትነት የውክልና ሥልጣንን (CPOA) ማስረጃ ካቀረበ ከክብካቤ ሰጪው ሌላ ተጨማሪ ነገር CFSA የመፈለጉ ዕድል በጣም አነስተኛ ነው፤ እና CFSA ምናልባት የእርስዎን ልጆች ለእሳቸው ይለቅላቸዋል እና በእርስዎ ልጆች ክብካቤ ላይ እጁን ማስገባትን ሊያቆም ይችላል። የእርስዎ ልጆች ክብካቤ በእርስዎ እና በእርስዎ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ መካከል በምሥጢር የሚያዝ ጉዳይ ይሆናል።

CPOA ያለው ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ የሌልዎት ከሆነና ሆኖም ግን የእርስዎን ልጆች ለመንከባከብ ፍቀደኛ የሆነ የታመነ ዘመድ ወይም ጓደኛ ያልዎት ከሆነ እና እኚህ ግለሰብ እርስዎ በተያዙ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ CFSA ን ካነጋገሩ፣ በተጨማሪ CFSA የእርስዎን ልጆች ለእሳቸው ሊለቅላቸው የመቻል ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ሆኖም ግን የወንጀል ሪኮርድ ያለባቸው መሆናቸውን ወይም በልጅ ላይ ጥቃት በማድረስ ወይም በቸልተኝነት ተመርምረው የሚያውቁ መሆናቸውን ለማጣራት በእሳቸው ቤት ውስጥ የሚኖሩ የሁሉንም ዕድሜያቸው ከ 18 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች የበስተጀርባ ታሪክ ፍተሻን በመጀመሪያ CFSA ማድረግ ይኖርበት ይሆናል።

ወዲያውኑ መፈታት እንድችል ምን ማድረግ እችላለሁ?

ታስረው በሚቆዩበት ጊዜ ከቤተሰብ አባላት ጋር የመገናኘት ዕድል ላይኖርዎት በሚችል ሁኔታ በ ICE እስር ቤት ውስጥ ቢያንስ ለጥቂት ቀናት ታስረው እንዲቆዩ ሊገደዱ የመቻልዎት ዕድል ከፍተኛ ነው። ይህ አንዳንድ ጊዜ እንደ መያዝ [holding] በመባል የሚጠቀስ ሆኖ በእርስዎ ጉዳይ ላይ ምን ሊደረግ እንደሚችል ICE ከውሳኔ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ያጋጥማል። ስልክ ለመደወል ያልዎት መዳረሻ በጣም የተገደበ ሊሆን ይችል ይሆናል እና በእርስዎ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በጣም ትንሽ ወይም ከናካቴው ምንም ላይነገርዎት ይችል ይሆናል።

የ ICE መኮንኖች ባሉት ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ የእርስዎን ከእስር መፈታት እንዲወስኑ ልዩ ሥልጣን አላቸው። ICE በራስዎት ዋስትና ወደ ማኅበረሰቡ መልሰው እንዲቀላቀሉ ሊለቅዎት (ይህም ማለት በተሰጠዎት ቀነ ቀጠሮ መሠረት ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት ቃል ይገባሉ ማለት ነው) ወይም በዩናይትድ ስቴትስ ስለመቆየትዎ በቂ አሳማኝ ማስረጃ (ለምሳሌ የአሜሪካ ዜጋ የሆኑ ልጆች መኖር) እንዳለ እና እርስዎ ለማኅበረሰቡ ወይም ለበረራ አደጋ እንዳልሆኑ ሲታመን በዝቅተኛ የገንዘብ ዋስትና እንዲለቀቁ ሊወስን ይችላል። በመሆኑም፣ እርስዎ እርስዎ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት እንዳልዎት የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ፎቶኮፒዎች መያዝዎት በጣም አስፈላጊ ነው። ለመንግሥት ምንም ዓይነት ኦርጂናል ሰነዶችን አይስጡ! መልሰው አያገኙዋቸውም። የሚከተሉትን የመሳሰሉ ሰነዶችን ፎቶኮፒዎች ለ ICE ይስጡ፦

 • በአሜሪካ የተወለዱ የእርስዎ ልጆች የልደት ምስክር ወረቀቶች
 • እንደ ለሕፃናት መምጣት ተቀያሪ እርምጃ [Deferred Action for Childhood Arrivals (DACA)] ከሆነ ጉዳዩ የእርስዎ ልጆች በአሜሪካ ሕጋዊ አቋም እንዳላቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች
 • የእርስዎ ልጆች የትምህርት ቤት ሪኮርዶች
 • የእርስዎ ልጆች የሕክምና ሪኮርዶች -- በተለይ የእርስዎ ልጆች ቀጣይ የሕክምና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው የጤና ችግር ካለባቸው
 • እርስዎ በአሜሪካ ለረዥም ጊዜ እንደኖሩ የሚያረጋግጡ እንደ የታክስ ሪኮርዶች፣ የአገልግሎት ክፍያ መጠየቂያ ደረሰኞች፣ የባንክ ሒሳብ ሪኮርዶች፣ የሕክምና ሪኮርዶች፣ የመኪና ክፍያዎች፣ የኪራይ ስምምነቶች፣ የፍጆታ አገልግሎቶች ክፍያ መጠየቂያ ደረሰኞች ወዘተ የመሳሰሉ ማናቸውም እና ሁሉም ማስረጃዎች።
 • ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ስለ እርስዎ ጥሩ ባሕሪ እና ምን ያክል ጊዜ በአሜሪካ እንደቆዩ ማረጋገጫ የሚሰጡ ደብዳቤዎች

ማናቸውም በእንግሊዝኛ ያልተጻፉ ሰነዶች የብቃት ማረጋገጫ ባለው ተርጓሚ አማካይነት ወደ እንግሊዝኛ መተርጎም አለባቸው። ለእያንዳንዱ የተተረጎመ ሰነድ በተርጓሚው የተሰጠ የትርጉም ትክክለኛነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትን ያካትቱ። የትርጉም ትክክለኛነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ናሙና በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ክፍል 3 ላይ ማግኘት ይቻላል።

የነዚህ ሰነዶች ሁሉንም ፎቶኮፒዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ በእርስዎ ቤት ውስጥ ማስቀመጥዎትን እንዲሁም ድንገት ከታሰሩ የሚቻል ከሆነ የኤሌክትሮኒክ ቅጂ መያዝዎትን ማረጋገጥ ይኖርብዎታል። የእርስዎ የታመነ ሰው እርስዎ ወደ የታያዙበት የ ICE ቢሮ ሊያመጡልዎት እንዲችሉ ሰነዶቹ የት እንደተቀመጡ ማወቃቸውን ያረጋግጡ። በድጋሚ፣ ለ ICE በጭራሽ ኦርጂናል ሰነዶችን እንዳይሰጡ።

ከእስር ከተለቀቁ፣ በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት መቼ እና የት መቅረብ እንዳለብዎት የሚያብራራ ሰነድ ይሰጥዎታል። በጭራሽ ከችሎቱ መቅረት የለብዎትም። ከችሎቱ ከቀሩ፣ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው ባለመቅረብዎ ምክንያት ከአገር እንዲባረሩ ሊወስኑ ይችላሉ። ወደ ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጊዜ ጠበቃ የሌልዎት ከሆነ፣ ጠበቃ እስከሚያገኙ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥዎት ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው መጠየቅ ይችላሉ።

መታሰር

ካልተፈታሁስ?

ካልተፈቱ፣ ለቀጣይ የእስር ሂደት አና የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ችሎትን ቀን ለመጠበቅ ወደ የኢሚግሬሽን ወህኒ ቤት ማእከል ይወሰዳሉ። እርስዎን ICE ሊለቅዎት የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሁንም ሊኖሩ መቻላቸው እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ ጊዜ ላይ ግን አስተማማኝነቱ ይበልጥ ያነሰ ነው እና በእስር ላይ ሆነው ምናልባት ቀናትን ወይም ምናልባትም በርካታ ሳምንታትን ሊቆዩ ይችላሉ። ICE ለእርስዎ ከእስር መፈታት የገንዘብ ዋስትናን ሊፈቅድ እና ምን ያክል ገንዘብ ዋስትና ማስያዝ እንዳለብዎት ሊነግርዎት ይችል ይሆናል። ICE የዋስትና ገንዘቡን መጠን ካላስቀመጠ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ችሎት በሚቀርቡበት ጊዜ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው የዋስትና ገንዘቡን መጠን እንዲወስኑልዎት መጠየቅ ይችላሉ። ለ ICE ያሳዩዋቸው (ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ) ተመሳሳይ ሰነዶች ዋስትናን ለመጠየቅ ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛ ሊቀርቡለት ይችላሉ (በዋስትና ገንዘብ ላይ በኋላ ላይ ተጨማሪ ዝርዝር ተሰጥቷል)።

ካልተፈታሁ፣ እነሱን ለመያዝ ማንም ሰው ሳይመጣላቸው ቢቀር በእኔ ልጆች ላይ ምን ይፈጠራል?

በፍጥነት ካልተለቀቁ እና ምንም የተሾመ ክብካቤ ሰጪ፣ ቤተሰብ አባል፣ ወይም ጓደኛ CFSA ን ሳያነጋግር ከቀረ፣ CFSA የእርስዎን ልጆች ይወስዳቸው እና የእርስዎን ልጆች ለመንከባከብ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ፍቃደኛ የሆነ ዘመድ ወይም የቤተሰብ ጓደኛን ለማግኘት ሥራውን መሥራት ይጀምራል።

የእርስዎ ልጆች ያሉት ከጓደኛ ወይም ከቤተሰብ አባል ጋር አይደለም ብለው ካሰቡ እና በ CFSA ቁጥጥር ሥር ያሉ ከሆኑ፣ ለእርስዎ ከአገር አሰናባች መኮንን በመንገር ከ CFSA ጋር ወዲያውኑ መነጋገር ይኖርብዎታል። CFSA የ 24 ሰዓት፣ ነጻ የስልክ መሥመር 202-671-SAFE (202-671-7233) አለው። ረጋ ይበሉ ሆኖም ግን የሚፈልጉትን ነገር ሳያሰልሱ ይናገሩ፣ እንዲሁም የእርስዎ ልጆች ደህና መሆናቸውን ለማረጋገጥ ማናቸውንም ማድረግ የሚቻል ነገር ሁሉ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ያብራሩ።

ስልክ ሲደውሉ፦

 • ሙሉ ስምዎትን ይናገሩ እና ራስዎን ወላጅ እንደሆኑ በግልጽ ያስታውቁ።
 • የእርስዎን ልጆች ሙሉ ስሞች እና የልደት ቀናት ይናገሩ።
 • እርስዎ በኢሚግሬሽን ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ እና የእርስዎ ልጆች በ CFSA ቁጥጥር ሥር ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ያስረዱ።
 • በእስር ቤት ውስጥ ሆነው የስልክ ጥሪዎችን መቀበል እንደማይችሉ፣ ይህ ድንገተኛ አደጋ ሁኔታ መሆኑን እና CFSA የተከፈተ ፋይል ያለው መሆኑን ማወቅ እንደሚፈልጉ በጣም ግልጽ ሆነው ያስረዱ።
 • የሾሙት ያልዎት ከሆነ የእርስዎን ክብካቤ ሰጪ ስም እና መገኛ አድራሻ መረጃ ይስጡ ወይም የሌልዎት ከሆነ የእርስዎን ልጆች ለመንከባከብ ፍቃደኛ ሊሆን እና ሊንከባከብ ይችላል ብለው የሚያምኑትን ሌላ የሚታመን ግለሰብ ስም እና መገኛ አድራሻ መረጃ ይስጡ።
 • የእርስዎን A Number እና እርስዎ የሚገኙበትን የወህኒ ቤት ማእከል ስም እና መገኛ አድራሻ ይስጡ።
 • የነጻ የስልክ መሥመር ሠራተኛዋ ይህን መረጃ ለ CFSA ትሰጣለች።

 

CFSA የእርስዎን ልጆች ከያዘ በዲሲ የቤተሰብ ፍርድ ቤት በ 72 ሰዓታት ውስጥ በመቅረብ የቸልተኝነት ወንጀል ክስን ፋይል እንዲያስገባ በሕግ ይገደዳል። የተሾመ የክብካቤ ሰጪ ካልዎት፣ ይህ ግለሰብ የቸልተኝነት ወንጀል ክስ ፋይል ከመከፈቱ በፊት ከ CFSA ጋር መነጋገሩ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ጊዜ የክስ ፋይል ከተከፈተ በኋላ እርስዎ እና የእርስዎ ልጆች የቸልተኝነት ወንጀል የፍርድ ክርክር የሚባለው የቤተሰብ ፍርድ ቤት ጉዳይ አንድ አካል ትሆናላችሁ እና የእርስዎ ልጆች ወደ እርስዎ ወይም ወደ የእርስዎ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ እንዲመለሱ ከመደረጉ በፊት በፍርድ ክርክሩ ማለፍ ይኖርባችኋል።

የቸልተኝነት ወንጀል ክስ የፍርድ ክርክር የእርስዎ ልጆች ከማን ጋር ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ እና ከማን ጋር እንደሚኖሩ ጨምሮ የቤተሰብ ፍርድ ቤቱ በእርስዎ ልጆች ላይ ለፈለገው አካል ሥልጣንን ይሰጣል። ምንም እንኳ የቸልተኝነት ወንጀል ክስ ተቀዳሚ ግቦች ከሆኑት መካከል ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር መልሰው እንዲቀላቀሉ ማድረግ ቢሆንም፣ ለበርካታ ዓመታት ሊቆይ የሚችል የተወሳሰበ የፍርድ ክርክር ሂደት ሊሆን ይችላል እንዲሁም የእርስዎን ልጆች እንደ ወላጅ የማሳደግ መብትዎን ሙሉ በሙሉ በስተመጨረሻ ሊያሳጣዎት የሚችልም ይሆናል። በድጋሚ፣ አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ይህ ነው።

CFSA የእርስዎን ልጆችን የሚንከባከብን የሆነ ሰው ለይቶ ማወቅ ካልቻለ ከማደጎ ወላጅ ጋር እንዲኖሩ ሊላኩ ይችላሉ። የማደጎ ወላጅ ሥልጠና የተሰጣቸው እና ልጆች ወላጆቻቸው እንክብካቤ ሊያደርጉላቸው ሳይችሉ ቢቀሩ ለልጆች ክብካቤ ለመስጠት ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው ሰው ናቸው። ዕድሜያቸው ትልቅ የሆኑ ልጆች በቡድን ቤት ውስጥ ሊመደቡ ይችላሉ - የቡድን ቤት ማለት ወላጆቻቸው ለእነርሱ ክብካቤ ሊያደርጉላቸው የማይችሉ በርካታ ዕድሜያቸው ትልቅ የሆኑ ልጆች አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሚቆጣጠራቸው ዐዋቂ ሰው አብሯቸው የሚኖርበትና ልጆቹ አንድ ላይ የሚኖሩበት መኖሪያ ነው።

የእኔን ልጆች በእኔ ቁጥጥር ሥር እንዳቆያቸው የሚያግዘኝ ጠበቃ ይኖረኛል?

የቸልተኝነት ወንጀል ክስ ፋይል ከተከፈተ ሕጋዊ የሆነ የኢሚግሬሽን አቋም ቢኖርዎትም ባይኖርዎትም በቸልተኝነት ወንጀል ክሱ የፍርድ ክርክር ሂደት ላይ እርስዎን የሚወክልዎትን ጠበቃ በፍርድ ቤቱ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ ይመደብልዎታል። የቤተሰብ ሕግ ጠበቃው በኮሎምቢያ ዲስትሪክት ይከፈለዋል -- እርስዎ ለዚህ ጠበቃ ክፍያ መፈጸም አይኖርብዎትም። የእርስዎ ቤተሰብ የሕግ ጠበቃ የእርስዎን ቋንቋ መናገር መቻለ አለበት። ይህን የቸልተኝነት ወንጀል ክስ የፍርድ ክርክርን ለእርስዎ ማስረዳትና ማብራራት፣ ስለ የእርስዎ ጉዳይ ወቅታዊ መረጃ መስጠት እና እንደ ወላጅ የእርስዎ መብቶች እንዲከበሩ ማስደረግ የዚህ ጠበቃ የሥራ ግዴታ ነው።

በቸልተኝነት ክስ ላይ ሌላ ማን እጁ ይኖርበታል?

ከእርስዎ የቤተሰብ ሕግ ጠበቃ በተጨማሪ የእርስዎን ልጆች ለመወከል በእርስዎ ላይ ምንም ወጪን ሳያስከትል እንዲሁ በተመሳሳይ በኮሎምቢያ ዲስትሪክት የሚከፈለው ጠበቃን የቤተሰብ ፍርድ ቤት ዳኛው ይሾማል። የእርስዎን ልጆች የተሻለ ጥቅም ማስጠበቅ የዚህ Guardian ad Litem (GAL) የሚባለው ጠበቃ የሥራ ግዴታው ነው። ማን የእርስዎን ልጆች መንከባከብ እንዳለበት እና እርስዎን እንዴት ልጆችዎ ወይም ሌሎች የእርስዎ ቤተሰብ አባላት ሊያዩዎት እንደሚችሉ ለቤተሰብ ፍርድ ቤት ዳኛው GAL የጥቆማ ሐሳቦችን እና ምክሮችን ይሰጣል። በልጅዎችዎ ሕይወት ላይ በጣም ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መቆየት እንዲችሉ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግዎ በጣም ወሳኝነት አለው። በፍርድ ክርክሩ ሂደት ላይ ለሚያጋጥሙ ማናቸውም ትላልቅ የሕክምና፣ የሥነ አእምሮ ወይም የትምህርት ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን እንዲሰጡ ለእርስዎ ይፈቀድልዎታል። GAL እና የእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ ከእርስዎ ልጆች ጋር ዳግመኛ አብረው መሆን እንደሚፈልጉ እና ይህ እንዲሆን ማናቸውንም ማድረግ የሚቻል ነገር ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንዎትን እንዲያውቁ ያድርጉዋቸው።

ከእርስዎ GAL ጋር ሲነጋገሩ ሁልጊዜ ረጋ ይበሉ እና ትዕግሥት ይኑርዎት። እርስዎ ስልክ ሲደውሉ GAL መልስ ካልሰጠ፣ በተቻልዎት መጠን በጉዳዩ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ መሆንዎትዎን ለማረጋገጥ እንዲችሉ መልእክት ይተዉላቸው። ሁልጊዜ የደወሉበትን ቀን እና ሰዓት በመልእክቱ ላይ ምን እንዳሉ በወረቀት ጽፈው ያስቀምጡ። በተቻለ ፍጥነት የእርስዎ ልጆች ከእርስዎ ጋር መሆናቸው ለእነርሱ የተሻለ መሆኑን GAL እንዲያውቀው ማድረግ የእርስዎ ግዴታ ነው።

CFSA በተጨማሪ በእርስዎ ጉዳይ ላይ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛ [caseworker] ይመድባል። የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ለእሳቸው እርስዎ እና የእርስዎ ልጆች ምን እንደነገራችኋቸው ለቤተሰብ ፍርድ ቤት ዳኛው ይነግራሉ እንዲሁም ለእርስዎ ልጆች ማን እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት እና ስለ ጉብኝት ምክሮችን እና ጥቆማ ሐሳቦችን ይሰጣሉ። በእንግሊዝኛ የመግባባት ችግር ካለባችሁ እርስዎ እና የእርስዎ ልጆች የእርስዎን ቋንቋ የሚናገር ተባባሪ ሠራተኛ እንዲመደብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ። ተባባሪው ሠራተኛ ለእርስዎ እና ለእርስዎ ልጆች እንደ ሁኔታው አስፈላጊነት አገልግሎቶችን እንድታገኙ ጥቆማ ሐሳብ በተጨማሪ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ከእሳቸው ጋር በመደበኛነት እና በግልጽነት መግባባት በጣም አስፈላጊ ነው።

ልክ ከ GAL እንደሚያደርጉት፣ በሁሉም ነገር ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መቆየት እና ከልጆችዎ ጋር መልሰው አንድ ላይ መሆን እንዲሁም ይህም እንዲሆን ማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንዎትን የእርስዎ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛ እንዲያውቁት ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግዎ በጣም አስፈላጊ ነው። ከእርሳቸው ጋር ሲነጋገሩ ረጋ ይበሉ እና ትዕግሥት ይኑርዎት። እርስዎ ስልክ ሲደውሉ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛ መልስ ካልሰጡዎት፣ በተቻልዎት መጠን በልጆችዎ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ መሆንዎትዎን ለማረጋገጥ እንዲችሉ መልእክት ይተዉላቸው። ለጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ሁልጊዜ የደወሉበትን ቀን እና ሰዓት በመልእክቱ ላይ ምን እንዳሉ በወረቀት ጽፈው ያስቀምጡ። ከጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ጋር መገናኘት ካልቻሉ፣ ለእሳቸው ኃላፊ ይደውሉና ይንገሩዋቸው ወይም ለእሳቸው ልክ ለጉዳይ ክትትል ሠራተኛው የሚነግሯዋቸውን ነገሮች በመንገር መልእክት ይተዉላቸው። የኃላፊው ስም እና የስልክ ቊጥር በጉዳይ ክትትል ሠራተኛው የድምፅ መልእክት ላይ መጠቀስ አለበት።

በዚህ ሁኔታ ላይ የእርስዎን ጉዳይ የሚይዘው ብቸኛው ሰው የእርስዎ ቤተሰብ የሕግ አማካሪ ጠበቃው ነው። የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው እና GAL የግድ የእርስዎ ተባባሪዎች መሆን የለባቸውም እና ልጆችዎ ከእርስዎ ይልቅ ከሌላ ሰው ጋር ቢሆኑ ለልጆችዎ የተሻለ ይሆናል ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት፣ ከ GAL እና ከጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ጋር የሚያደርጉዋቸውን የመልእክት ልውውጦች ሪኮርድ መያዝዎት እና ይህን መረጃ ከእርስዎ ቤተሰብ የሕግ አማካሪ ጠበቃ ጋር መካፈልዎት በጣም አስፈላጊ ነው። 

 

በ ICE ታስሮ የነበረ ሰውን እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

በዲሲ-ሜሪላንድ-ቨርጂኒያ (DMV) አካባቢ ቢያንስ አምስት የወህኒ ቤት ተቋማት አሉ። ምናልባት እርስዎ በሜሪላንድ ወይም በቨርጂኒያ ውስጥ በሚገኝ ወህኒ ቤት ውስጥ ሊታሰሩ ይችሉ ይሆናል ሆኖም ግን በማናቸውም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኝ ወህኒ ቤት ውስጥ ሊያዙ ወይም በተለያዩ ወህኒ ቤቶች ውስጥ እንዲዘዋወሩ ሊደረጉ ይችሉ ይሆናል። የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪዎች በተለምዶ በመጀመሪያ ሊወሰዱ የሚችሉባችውን ወህኒ ቤቶችን በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ክፍል 3 ላይ ሊያገኙዋቸው ይችላሉ።

በተጨማሪ “የICE እስረኛ ማግኛ” ["ICE detainee locator"] የተባለ በ ICE የተያዙ ሰዎችን መፈለግ ለሚፈልግ ሰው እገዛ የሚሰጥ ድረ-ገጽ https://locator.ice.gov/odls/homePage.do ላይ ይገኛል። ይህን የድር ጣቢያ ለመጠቀም፣ የታሳሪውን ስም ልክ በ ICE እንደተጻፈው አድረገው መጻፍ (ምንም እንኳ የተጻፈው በመጀመሪያ በስህተት እንኳ ቢሆን) እንዲሁም የግለሰቡን የልደት ቀን እና ምንጭ አገር፣ ወይም የግለሰቡን የኢሚግሬሽን መለያ ቊጥር የሆነው A number ማስገባት ይኖርብዎታል። እርስዎ በ ICE ከተያዙ የቤተሰብ አባላት እርስዎን ሊያገኙ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ነው።

የከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን ሚናው ምንድን ነው?

ከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን ለእርስዎ ይመደብልዎታል። ለእርስዎ ከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንንን ወዲያውኑ ስለ የእርስዎ ልጆች እና እርስዎ ካልተለቀቁ ማን የእርስዎን ልጆች እንደሚያዛቸው እንደሚያሳስብዎት መንገር አለብዎት። የእርስዎ የከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን ለ ICE ይሠራል እንዲሁም እርስዎ በእስር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ የእርስዎ ጉዳይ ኃላፊ ነው። መኮንኑ እርስዎ በእስር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ በቀጣይነት ከእርስዎ ጋር መገናኘት አለብዎት። የመኮንኑ ግዴታ የእርስዎን ከአገር ማስወጣት የሥራ ሂደት ማሳለጥ ነው። እሳቸው ተቀጣሪነታቸው ለ ICE እንደመሆኑ፣ የእርስዎ ከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንንን ለእርስዎ ስለ የእርስዎ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ጠቃሚ ምክር ሊሰጥዎት በሚያስችላቸው አቋም ላይ አይገኙም።

የኢሚግሬሽን ጠበቃ እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ያልተያዙ በሲቪል ሕግ መሠረት በ ICE የተያዙ እንደመሆንዎት መንግሥት የኢሚግሬሽን ጠበቃ ለእርስዎ አያቀርብልዎትም። የኢሚግሬሽን ጠበቃ ለመቅጠር በራስዎት አቅም የሌልዎት ከሆኑ ለትርፍ ካልቆመ ሕጋዊ የእርዳታ ድርጅት በነጻ የኢሚግሬሽን ጠበቃ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል። ለትርፍ ያልቆሙ ሕጋዊ የእርዳታ ድርጅቶች ዝርዝር በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ክፍል 3 ላይ ማግኘት ይቻላል። መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ፣ ሕጋዊ ጠበቃ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ይልቅ ቊጥራቸው የበዛ በርካታ የኢሚግሬሽን ጠበቃ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አሉ። ጠበቃ በነጻ ማግኘት የማይችሉ ከሆነ፣ በግልዎ ጠበቃ መቅጠር እና ክፍያውን መፈጸም ወይም የእርስዎ ቤተሰብ እንዲቀጥርልዎት እና እንዲከፍልልዎት ማድረግ ይኖርብዎታል። ሆኖም ግን ጠበቃ ማግኘት ካልቻሉ፣ ብቻዎትን አይቀሩም። አብዛኛዎቹ በኢሚግሬሽን ወህኒ ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች በስተመጨረሻ ጉዳያቸውን ራሳቸው ያለጠበቃ ይከራከራሉ።

የኢሚግሪሽን ጠበቃ ነን የሚሉ አስመሳይ አጭበርባሪዎች እንዳይታለሉ ይጠንቀቁ። ቊጥራቸው ብዙ የሆኑ የኢሚግሬሽን ጠበቆች አሉ። መጥፎ ዕድል ሆኖ ግን በእስር ቤት ባሉ ሰዎች በማታለል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ጠበቃ ነን ባዮችም አሉ። አንዳንድ የኢሚግሬሽን ጠበቆች ምንም እንኳ በሕግ እርስዎን ሊያግዝዎት የሚችሉት በጣም ትንሽ ነገር ቢሆንም የእርስዎን ገንዘብ ከመውሰድ ግን ወደኋላ አይሉም። እርስዎን እንዲወክልዎት የግል ኢሚግሬሽን ጠበቃ እርስዎ ወይም የእርስዎ ቤተሰብ አባል ልትቀጥሩ ከሆነ የራሳችሁን የቤት ሥራ በመጀመሪያ ሥሩ እንዲሁም ስለሚሰጡት አገልግሎት ጥራት ደረጃ ማወቅ እንድትችሉ የኢሚግሬሽን ጠበቃው ዋቢ የሚሆኑ ሰዎችን እንዲጠቅሱልዎት ይጠይቁዋቸው።

በተጨማሪ፣ “የሕዝብ አዋዋይ” ["notario" ] የእርስዎ ጠበቃ ወይም ሕጋዊ ወኪል እንዲሆኑ አይቅጠሩ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ፣ “የሕዝብ አዋዋይ” ["notario"] የግድ የብቃት ማረጋገጫ ያለው ጠበቃ መሆን የለበትም። በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ የሕዝብ አዋዋይ ["notario"] የሚለው ቃል የሕግ ትምህርት እና ልምድ ያለውን ሰው ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ቃል ነው። በዩኤስ አሜሪካ ግን የሕዝብ አዋዋይ ["notario"] ጠበቃ አይደለም፤ የሕዝብ አዋዋይ ["notario"] ዝምብሎ “የሕዝብ አዋዋይ” ["notary public"] (ሕዝብን የሚያዋውል፣ ወይም የአንድን ሰነድ ወይም ፊርማ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሰው) ነው። የሕዝብ አዋዋይ ["notario"] ወይም ["notary public"] በዲሲ ውስጥ ለመሆን መሟላት የሚያስፈልገው መስፈርት ግለሰቡ ዕድሜው ከ 18 ዓመት መሆን፣ በዲሲ ውስጥ መኖር፣ በእንግሊዝኛ ማንበብ፣ መጻፍ እና መናገር መቻል እንዲሁም ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ ኖሮበት ሆኖ አለማወቅ ነው -- ምንም ሕጋዊ ሥልጠናን መውሰድ አያስፈልገውም።

እኔ ከታሰርኩ በኋላ የዋስትና መብት ማግኘት እችላለሁ?

ከታሰሩ በኋላ አሁንም ድረስ የገንዘብ ዋስትና መክፈል እና ለመፈታት ዕድሉ ሊኖርዎት ይችል ይሆናል። ሁሉም ሰው የገንዘብ ዋስትናን ለማስያዝ ብቁ አይደለም ስለዚህ ለእርስዎ የገንዘብ ዋስትና አማራጭ እንዳልዎት የእርስዎን ከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን ወይም የኢሚግሬሽን ጠበቃን ይጠይቁዋቸው። ICE ወይም የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤቱ ለእርስዎ ሊሰጥዎት የሚችሉት ዝቅተኛው የዋስትና ማስያዣ የገንዘብ መጠን ብዙውን ጊዜ $1,500 ሲሆን አብዛኛዎቹ ምንም የወንጀል ሪኮርድ የሌላቸው ሰዎች ከ $3,000 እስከ $7,500 ድረስ የዋስትና ገንዘብን እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ። ከእስር እንዲለቀቁ የዋስትና ገንዘቡን በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲከፍሉ አይገደዱም። ምናልባት እርስዎ በ ICE ቢያዙ እንደሚያደርጉት የጥንቃቄ ዝግጅት ወይም ዕቅድ አንድ አካል፣ እርስዎ ከታሰሩ እርስዎ ወይም የእርስዎ ቤተሰብ አባላት እንዴት የዋስትና ገንዘብን መክፈል እንደምትችሉ ማሰብ አለብዎት። ለእርስዎ ዋስትና ማስያዣ በጥሬ ገንዘብ መክፈል እንዲችሉ ገንዘብ ቆጥቦ ማስቀመጥን እንደ አማራጭ ሊይዙት ይችላሉ። በተጨማሪ በዋስትና ጠለፋ ሰጪ ኩባንያ በኩል የእርስዎን የዋስትና ማስያዣ ገንዘብ ለመክፈል ይችላሉ ሆኖም ግን የዋስትና ጠለፋ ሰጪ ኩባንያን የሚጠቀሙ ከሆኑ እንደዚህ የመሳሰሉ ኩባንያዎች አንዳንድ ጊዜ ከባድ ወለድን እንዲከፍሉ ወይም ከተፈቱ በኋላ በእግር ላይ የሚታሰር እግረ ሙቅን እንዲያደርጉ ሊያስገድድዎት ስለሚችሉ ይጠንቀቁ።

የዋስትና ችሎት እንዲቆምልኝ ለመጠየቅ እንዴት ማድረግ እችላለሁ?

የዋስትና ገንዘብ በማቅረብ መፈታት አማራጭ ያልዎት መሆኑን እርግጠኛ ካልሆኑ የዋስትና ችሎት እንዲቆምልዎት የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛውን መጠየቅ አለብዎት። ስለ የእርስዎ ልጆች ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው መንገርዎትን እና እነርሱን ለመንከባከብ እና እነርሱን ለመያዝ መፈታት እንደሚፈልጉ መንገርዎትን እርግጠኛ ይሁኑ።

በችሎቱ ላይ፣ እንደሚከተሉት የመሳሰሉ ከዚህ በላይ የተነጋገርንባቸውን ሰነዶች እርስዎ ለማኅበረሰቡ ወይም ለበረራ አደጋ አለመሆንዎትን ለማሳየት (በጭራሽ ኦርጂናል ሰነዶችን አይስጡ!) የሰነዶቹን ፎቶኮፒዎች ማቅረብ አለበዎት፦

በአሜሪካ የተወለዱ የእርስዎ ልጆች የልደት ምስክር ወረቀቶች

 • እንደ ለሕፃናት መምጣት ተቀያሪ እርምጃ [Deferred Action for Childhood Arrivals (DACA)] ከሆነ ጉዳዩ የእርስዎ ልጆች በአሜሪካ ሕጋዊ አቋም እንዳላቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች
 • የእርስዎ ልጆች የትምህርት ቤት ሪኮርዶች
 • የእርስዎ ልጆች የሕክምና ሪኮርዶች -- በተለይ ከእርስዎ ልጆች ማናቸውም ቀጣይ የሕክምና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው የጤና ችግር ካለባቸው
 • እርስዎ በአሜሪካ ለረዥም ጊዜ እንደኖሩ የሚያረጋግጡ እንደ የታክስ ሪኮርዶች፣ የአገልግሎት ክፍያ መጠየቂያ ደረሰኞች፣ የባንክ ሒሳብ ሪኮርዶች፣ የሕክምና ሪኮርዶች፣ የመኪና ክፍያዎች፣ የኪራይ ስምምነቶች፣ የፍጆታ አገልግሎቶች ክፍያ መጠየቂያ ደረሰኞች ወዘተ የመሳሰሉ ማናቸውም እና ሁሉም ማስረጃዎች።
 • ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ስለ እርስዎ ጥሩ ባሕሪ እና ምን ያክል ጊዜ በአሜሪካ እንደቆዩ ማረጋገጫ የሚሰጡ ደብዳቤዎች

ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው፣ ማናቸውም በእንግሊዝኛ ያልተጻፉ ሰነዶች የብቃት ማረጋገጫ ባለው ተርጓሚ አማካይነት ወደ እንግሊዝኛ መተርጎም አለባቸው። ለእያንዳንዱ የተተረጎመ ሰነድ በተርጓሚው የተሰጠ የትርጉም ትክክለኛነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀትን ያካትቱ። የትርጉም ትክክለኛነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ናሙና በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ክፍል 3 ላይ ማግኘት ይቻላል።

ከእስር ልፈታ የምችልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ?

የእርስዎ ጉዳይ ለ ICE ከፍተኛ ተቀዳሚነት የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ እና እርስዎ መታሰር ያለብዎት ዓይነት ሰው ባለመሆንዎት -- እርስዎ ምንም ዓይነት የወንጀል ሪኮርድ የሌለብዎት ስለሆነ እና በዩኤስ አሜሪካ ውስጥ ጥገኛ ሆነው እገዛ ማግኘት የማያስፈልግዎት ሰው ስለሆኑ እርስዎ ከእስር እንዲፈቱ የሰብአዊ ምህረት [Humanitarian Parole] እና የዓቃቤ ሕግ በጎ ፈቃድ [Prosecutorial Discretion] ጥያቄዎች ይቀርባሉ። ብቁ ሆነው ከተገኙ፣ ለእርስዎ ከአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን እና ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው ሰብአዊ ምህረት እና የዓቃቤ ሕግ በጎ ፈቃድ ከእስር እርስዎ እንዲፈቱ ወይም በእርስዎ ላይ የቀረበው ክስ ተዘግቶ በነጻ እንዲሰናበቱ እንዲደረጉ እንደሚፈልጉ መንገር ይችላሉ።

ልክ የዋስትና ገንዘብ በማቅረብ ለመፈታት እንዳደረጉት ሁሉ ሰብአዊ ምህረትን እና የዓቃቤ ሕግ በጎ ፈቃድን ለመጠየቅ (ከዚህ በላይ እንደተዘረዘሩት) ተመሳሳይ ሰነዶችን መጠቀም ይችላሉ። በድጋሚ፣ ለእርስዎ የአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንንን ወይም ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው የነዚህን ሰነዶች ፎቶ ኮፒዎች ብቻ መስጠዎትን እርግጠኛ ይሁኑ እና ኦርጂናሎቹን ደኅንነቱ አስተማማኝ በሆነ ቦታ ላይ ያስቀምጡት።

ለእኔ ከአገር እንድወጣ የሚደረግ እርምጃ ላይ እንድፈርም ብደረግስ?

በ ICE ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ፣ መኮንኖች የሚፈረሙ ወረቀቶችን እየያዙ ወደ እርስዎ ሊመጡ ይችሉ ይሆናል። ይህ የሚፈረም ሰነድ በርካታ ጊዜ ለእርስዎ በተለያዩ መኮንኖች ሊቀርብልዎት ይችል ይሆናል። ምንም የክስ ፋይል እንደሌለብዎት፤ ለእርስዎ ከአገር መባረር መፈረም እንዳለብዎት፣ ወዲያውኑ ካልፈረሙ ለዓመታት በእስር ቤት ታስረው እንደሚቆዩ እና የእርስዎን ልጆች ዳግመኛ እንደማያዩዋቸው ሊነገርዎት ይችላል። አንድ መኮንን ጉልበት ሁሉ ተጠቅሞ በወረቀት ላይ ሊያስፈርምዎት ሊያስገድድዎት ይችል ይሆናል። ምን እንደሆነ ሳይገባቸው በግድ በሰነድ ላይ እንዲፈርሙ እንደተገደዱ በርካታ ወላጆች ሪፖርት አድርገዋል።

እነዚህን ሰነዶች ለመፈረም ከተስማሙ እና ከአገር መባረርን ከተቀበሉት ወደ አሜሪካ ተመልሰው መምጣት እና ልጆችዎን መልሶ ለማግኘት ለመታገል ለእርስዎ የማይቻል ነገር ይሆንብዎታል። ከአገር መባረርን በመቀበል በማናቸውም ሰነድ ላይ ላለመፈረም አሻፈረኝ ለማለት መብት አልዎት። በእስር ቤት ተጨማሪ ጊዜ ለመቆየት መስማማት ማለት ሊሆን ስለሚችል ይህ ከባድ ውሳኔ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን የእርስዎን ከአገር መባረር በመስማማት ከፈረሙ ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛ የእርስዎን ጉዳይ ለማቅረብ አይችሉም።።

ሆኖም ግን በራስዎ ዋስትና ከእስር እንደሚለቀቁ የሚናገር ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ሰነድ ከቀረበልዎት (ማለትም በተሰጥዎት ቀነ ቀጠሮ ወደ ፍርድ ቤት ራስዎ እንደሚመጡ ቃል ከገቡ) እንዲፈቱ በዚህ ሰነድ ላይ የግድ መፈረም ይኖርብዎታል። ሆኖም ግን ከመፈረምዎ በፊት በእንግሊዝኛ አንብቦ ለመረዳት ችግር ካለብዎት በእርስዎ አፍ መፍቻ ቋንቋ ለእርስዎ እንዲብራራልዎት ማስደረግዎን እርግጠኛ ይሁኑ!

የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ሂደት እንዴት ይሠራል እና እንዴት ስለ የእኔ ጉዳይ መታገል እችላለሁ?

ዋና የቀን መቊጠሪያ ቀን ችሎት [Master Calendar Hearing] በመባል የሚታወቀውን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛ ፊት ከመቅረብዎ በፊት ለሳምንታት ሊታሰሩ ይችሉ ይሆናል። በዚህ ችሎት ላይ ልክ እርስዎን የመሳሰሉ ሌሎች እስረኞች ይኖራሉ እና ከኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው ጋር ለመነጋገር እርስዎ በተናጠል ወይም በቡድን ሊጠሩ ይችሉ ይሆናል። የእርስዎ ችሎት ላይ ምን ቋንቋን መጠቀም እንደሚፈልጉ ይጠየቃሉ። በስፓኒሽኛ ለመናገር እንዲችሉ በዚህ ችሎት ላይ አስተርጓሚ የሚገኝ ይሆናል። አገር በቀል ቋንቋዎችን ጨምሮ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ከሆኑ፣ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው በስልክ አስተርጓሚ ይጠቀማል። አስተርጓሚውን መረዳት ካልቻሉ፣ ይህንኑ ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው መንገርዎት አስፈላጊ ሲሆን አስተርጓሚው እርስዎ ይበልጥ በግልጽ ተግባብተው ሊያናግሩት በሚችሉት ሌላ አስተርጓሚ እንዲቀየር ማድረግዎትን እርግጠኛ ይሁኑ።

የኢሚግሬሽን ጠበቃ ከሌልዎት፣ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው በመጀመሪያው ችሎት ላይ ምናልባት አንድ እስከሚያገኙ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልግዎት እንደሆነ ያለጥርጥር ሊጠይቅዎት ይችሉ ይሆናል። በተለይ ከእርስዎ ቤተሰብ ጋር መነጋገር ያልቻሉ ከሆነ ወይም ያልዎትን የዋስትና ገንዘብ ክፍያ ከፍሎ የመለቀቅ መብት ተጠቅመው ለመፈታት የሚያስችል አቅም እንዳልዎት የሚያስቡ ከሆነ ወይም የዋስትና ችሎት እንዲቆምልዎት ለማድረግ እየሞከሩ ያሉ ከሆኑ ወይም የኢሚግሬሽን ጠበቃ ለማግኘት ይችሉ እንደሆነ ለመጠየቅ እንዲችሉ የኢሚግሬሽን ጠበቃ እስከሚያገኙ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥዎት መጠየቅ ጥሩ ሐሳብ ነው።

ከዚህ የመጀመሪያው ችሎት በኋላ፣ ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ዋና የቀን መቊጠሪያ ቀን ችሎት [Master Calendar Hearing] የሚኖርዎት ሲሆን የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው እርስዎ ማናቸውም ዓይነት ሕጋዊ ፋታ ለማግኘት እያመለከቱ ያሉ እንደሆኑ ወይም በዩኤስ አሜሪካ ለመቆየት በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤቱ ማመልከቻ እያስገቡ ያሉ መሆንዎትን ይጠይቅዎታል። እነዚህ ሁሉ ቃላትና ሐረጎች በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት የእርስዎን ከአገር የማስወጣት እርምጃ የሚቃወሙ እና የሚከራከሩበት መሆን አለመሆንዎትን ይመለከታሉ። የግል የኢሚግሬሽን ጠበቃ ከቀጠሩ ወይም የኢሚግሬሽን ጠበቃ የሕግ ምክር እና አገልግሎት ያልዎት ከሆኑ የእርስዎን ከአገር መባረር ጉዳይ በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ቀርበው ለመከራከር የሕግ መሠረት እንዳልዎትና እንደሌልዎት ተጨማሪ መረጃን ያገኛሉ። የእርስዎን ከአገር መባረር ጉዳይ በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ቀርበው የሚከራከሩ ከሆነ፣ በማስረጃ፣ በእማኞች፣ እና በራስዎ የእምነት ቃል ተጠቅመው የእርስዎን ጉዳይ ለኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛው የሚያቀርቡበት የመልካምነት ችሎት [Merits Hearing] ወይም የግለሰብ ችሎት [Individual Hearing] ይቆምልዎታል።

እያንዳንዱ የፍርድ ቤት ጉዳይ ራሱን የቻለ እና የተለያየ ነው፣ ሆኖም ግን በዚህ የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ሂደት ውስጥ ሲያልፉ ሰዎች ለበርካታ ወራት ታስረው ሊቆዩ ይችላሉ። በተለይ እርስዎ ይህን ሁሉ ጊዜ ለልጆችዎ ተነጥለው እንዲታሰሩ የሚደረጉ ከሆነ በጣም አስጨናቂ እንዲያውም አሜን ብሎ ለመቀበል አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ግን የእርስዎን ከአገር መባረር ለመከራከር ብቸኛው አማራጭዎ ይህ እንደሆነ መገንዘቡ ግን በጣም አስፈላጊ ነው። በዋና የቀን መቊጠሪያ ችሎት [Master Calendar Hearing] ላይ ወይም ለአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንኑ ከአገር የማስወጣት እርምጃውን እንደሚቀበሉ ካረጋገጡ፣ የእርስዎን ልጆች በኋላ ላይ ተመልሶ በመምጣት ለማግኘት ክርክር ለማድረግ የማይቻል ነገር ይሆናል (እርስዎ ከአገር እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ ወደ ራስዎ አገር ቤት ልጆችዎን ለማስመጣት ግን ይችላሉ -- እዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ በኋላ ላይ ይሰጣል)።

የእኔን ልጆች መያዝ እንድችል ከእስር ለማምለጥ ምን ማድረግ እችላለሁ?

በተቻለ መጠን ከእርስዎ ልጆች ጋር ቅርብ ትስስር እና ግንኙነት እንዳልዎት ሆነው መቆየት አለብዎት። ለእነርሱ ደብዳቤዎችን መጻፍ አለብዎት። በእስር ቤት እያሉ እንኳ ቢሆን ከእነርሱ ደብዳቤዎችን እና ሥዕሎችን (ፎቶግራፎችን) ለመቀበል ይፈቀድልዎታል። ለእርስዎ ልጆች የሚልኩላቸውን ማናቸውንም ነገር በማስታወሻ ይያዙት እና ከእነርሱ የሚቀበሉዋቸውን ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ ያስቀምጡዋቸው። የእርስዎን ልጆች ሪፖርት ካርዶች ለማየት በተጨማሪ መጠየቅ እና የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው እንደ የጤና ችግሮች የመሳሰሉ ነገሮችን፣ የእርስዎ ልጆች ትምህርት ቤት እና የሚሳተፉባቸውን እንቅስቃሴዎች መለወጥ እንዳለባቸው የመሳሰሉ ነገሮችን በተመለከተ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲሰጥዎት መጠየቅ ይችላሉ።

ምንም እንኳ የማይመስል ነገር ቢሆንም፣ ከወህኒ ቤት የእርስዎን ልጆች ስልክ ደውለው ማናገር እንዲችሉ ከ CFSA የእርስዎን ልጆች የማደጎ አሳዳጊ ወላጅ ስልክ ቊጥርን ለማግኘት ይችሉ ይሆናል። ወይም የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ባለበት ወደ የእርስዎ ልጆች መደወል ይችላሉ። ለእነዚህ የስልክ ጥሪዎች የእርስዎ የአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን አስፈላጊውን መሰናዶ በማድረግ እርስዎን ማገዝ አለበት። ስልክ በደወሉ ቊጥር የደወሉበትን ሰዓት፣ ቀን እና ምን እንደተነጋገራችሁ በትንሹ በወረቀት ጽፈው ያስቀምጡ።

በሁሉም የቸልተኝነት ክስ ችሎቶች ላይ በአካል መገኘት አለብዎት። እርስዎ በወህኒ ቤት ታስረው እያለ በቸልተኝነት ክስ ችሎቶች ላይ በስልክ ለመሳተፍ መብቱ አልዎት። ይህ በስልክ ወደ ችሎት መቅረብ [telephonic appearance] ይባላል። በዚህ ችሎት ላይ መሳተፍ እንደሚፈልጉ የእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ እንዲያውቅ ማድረግዎትን እርግጠኛ ይሁኑ። ይህ የእርስዎን የአገር ማስወጣት እርምጃ መኮንን እና የእርስዎን የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ በማቀናጀት ሊዘጋጅ ይችላል። ICE እርስዎ በቸልተኝነት ክስ ችሎቱ ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ነጻውን የስልክ ጥሪ ማድረግ እንዲችሉ መነጋገሪያ ክፍል ያዘጋጅልዎታል።

ሐሳብ ማቅረቢያ ማመልከቻ በማስገባት ወይም ፈቃድ ለሚሰጠው ለቤተሰብ ጉዳይ ፍርድ ቤት ዳኛው በጽሑፍ ጥያቄ በማቅረብ የእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ ለችሎት ወደ የቤተሰብ ጉዳይ ሰሚ ፍርድ ቤት ICE እርስዎን እንዲያጓጉዝዎት እንዲያደርግ የቤተሰብ ጉዳይ ፍርድ ቤት ዳኛውን በተጨማሪ መጠየቅ ይችላል። ይህ የሚቻል ከሆነ፣ በአካል ተገኝቶ መሳተፉ ተመራጭ ነው።

ስለ የእርስዎ የኢሚግሬሽን ጉዳይ እና የሚቀጥለው የእርስዎ የኢሚግሬሽን ችሎት መቼ እንደሆነ ለሁሉም ሰው በተለይ ለእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ ወቅታዊ መረጃ መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። የእርስዎን የኢሚግሬሽን ጉዳይ መቼ እንደሚያበቃ እና መቼ ከእስር ቤት እንደሚፈቱ ለማወቅ በጣም ይጓጓሉ።

በችሎቱ ላይ መሳተፍ የማይችሉ ከሆነ፣ እነዚህን ማስተካከያዎች ለማድረግ ለእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ፣ ለ GAL፣ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለእርስዎ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛ ለምን በ ICE በኩል ያደረጉዋቸው ጥረቶች ለምን እንዳደረጉዋቸው ለማብራራት ደብዳቤ መጻፍ አለብዎት።

የቤተሰብ ጉዳይ ፍርድ ቤት ዳኛው እንደ በጉዳይ ክትትል ሠራተኛው በሚቀርበው ሐሳብ መሠረት በአገልግሎቶች ላይ መሳተፍ የመሳሰሉ የተወሰኑ ነገሮችን እንዲፈጽሙ የሚያዝ ትዕዛዝ በእርስዎ ላይ ሊሰጥ ይችል ይሆናል። በዚህ ትዕዛዝ ተገዢ ለመሆን ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ በእርስዎ አቅም የሚቻልዎትን ሁሉ ማድረግ አልብዎት እና ትዕዛዙን ለማክበር የማይችሉ ከሆነ ለእርስዎ ቤተሰብ የሕግ አማካሪ ጠበቃ፣ ለ GAL እና ለጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ይህንኑ ማሳወቅዎን እርግጠኛ ይሁኑ እና ትዕዛዙን ለማክበር ምን ጥረት እንዳደረጉ ይንገሩዋቸው።

 

እኔ በእስር ላይ ሳለሁ የእኔ ልጆች እኔን ለማየት ይፈቀድላቸዋል?

ለልጆችዎ የተሻለ የሚሆነውን ከግምት በማስገባት የእርስዎ ልጆች በወህኒ ቤት እርስዎን መጎብኘት መቻል አለመቻልዎን የመወሰን ሥልጣኑ የቤተሰብ ፍርድ ቤት ዳኛው ነው። ለአንዳንድ ልጆች ወላጅን በወህኒ ቤት ውስጥ ማየት ለዕድሜ ልክ በጭንቅላት ተቀብሮ የሚቀር አሰቃቂ ተሞክሮ ሊሆን ይቻላል። የእርስዎ ልጆች በወህኒ ቤት መጥተው እንዲያዩዎት ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ፣ ለእርስዎ ቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ፣ GAL፣ እና ለጉዳይ ክትትል ሠራተኛው መንገር አለብዎት። የእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ የቤተሰብ ጉዳይ ዳኛው ጉብኝት ፈቃድን እንዲያዝ በመጠየቅ ሐሳቡን በፋይል ማቅረብ ይችላል።

የቤተሰብ ፍርድ ቤት ዳኛው ጉብኝት እንዲደረግ ትዕዛዝ ከሰጠ፣ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ወይም እንደ የማደጎ ወላጅ ወይም ከእርስዎ ዘመዶች አንዱ የመሰለ ሌላ ፈቃድ የተሰጠው ዐዋቂ ሰው የእርስዎን ልጆች ወደ ወህኒ ቤቱ ሊያመጣቸው ይችላል። ICE ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ምንም እንኳ የማኅበራዊ ዋስትና ቊጥር ባይኖራቸውም እና ያላቸው ዜግነት ምን እንደሆነ ከግምት ሳይገባ ጉብኝት እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋል። ዐዋቂ ሰዎች ከጉብኝቱ በፊት የልደት ቀናቸውን እና የማኅበራዊ ዋስትና ቊጥራቸውን ለ ICE መስጠት እና በቅድሚያ ፈቃድ ማግኘት አለባቸው። ከእርስዎ ልጆች ጋር የሚመጡት ዐዋቂ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለመኖር ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነገር ነው -- አለበለዚያ ምንም እንኳ በዚያ የተገኙት እርስዎን ለመጎብኘት ቢሆንም በወህኒ ቤቱ ውስጥ በ ICE ሊያዙ ይችላሉ።

ልጅዎችዎ ሲጎበኝዎት “ምንም ዓይነት አካላዊ ንክኪ” ማድረግ አይፈቀድም። ይህ ማለት የእርስዎን ልጆች በመስኮት ውስጥ ያዩዋቸዋል እና በስልክ ሊያናግሩዋቸው ይችላሉ ሆኖም ግን የእርስዎን ልጆች ማቀፍ ወይም መያዝ አይችሉም። በተጨማሪ ከእነርሱ ምንም ነገር መቀበል እርስዎም ለእነርሱ ምንም ነገር መሰጠት አይችሉም ሆኖም ግን በመስኮቱ በኩል ፎቶዎችን ሊያሳይዎት ይችላሉ። እነዚህ ጉብኝቶች ምሥጢራዊነታቸው የተጠበቁ አይደሉም፤ ሌሎች ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ጉብኝት ሊያደርጉ ይችላሉ እና የእነርሱን ውይይት ሊሰሙ ይችሉ ይሆናል እንዲሁም እነርሱ የእናንተን ውይይትም ሊሰሙ ይችሉ ይሆናል። እነዚህ ጉብኝቶች በጣም አሳዛኝ ሊሆኑ ይችላሉ ሆኖም ግን የእርስዎን እንደ ወላጅ ያልዎትን ተሳትፎ በማስቀጠል ላይ እና በቤተሰብ ፍርድ ቤት ጉዳይ ላይ በጣም ወሳኝ የሆነ ሚና አላቸው።

ከአገር መባረር

እኔ ከአገር ከተባረርኩ የእኔን ልጆች ይዤ መሄድ እችላለሁ?

ከአገር እንዲባረሩ ከታዘዘ፣ እርስዎ ከአገር በሚባረሩበት ጊዜ የእርስዎን ልጆች እንዲይዙ አይፈቀድልዎትም እንዲሁም ለእርስዎ ልጆች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ጊዜ አይሰጥዎትም። ይህም ስለሆነ ነው ከአገር ከመባረር በፊት ዕቅድ ማውጣት እና አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አስቀድሞ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው። የመጡበት አገር ሜክሲኮ ከሆነ፣ እርስዎ በፈቃደኝነት ከአገር እንዲባረሩ ፊርማዎትን በፊርሙም ባይፈርሙም ወይም የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ዳኛ ከአገር እንዲባረሩ ቢወስንም ባይወስንም ልክ ወደ አገርዎ እንዲባረሩ ውሳኔ በተሰጠበት ቀን የዛኔውኑ የመላክ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው።

ከእርስዎ ቆንሲላ ጋር ለመነጋገር ዕድል ካገኙ ስለ የእርስዎ ልጆች ልትነግሩዋቸው እና ከእርስዎ ጋር አብረው እርስዎ ወደሚሄዱበት እንዲሄዱ የሚፈልጉ ከሆነ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግልዎት መጠየቅ አለብዎት። ቆንሲላው የእርስዎ ልጆች ከእነርሱ ተሿሚ ክብካቤ ሰጪ ጋር ወይም ከዘመድ ወይም ከጓደኛ ጋር ከሆኑ የጉዞ ዝግጅቶችን በማስተካከል ላይ ሊያግዝዎት ይችላሉ ሆኖም ግን ልጆችዎ ያሉት በማደጎ ክብካቤ ሥር ከሆነ ምንም ማድረግ አይችሉም። በዲሲ ውስት የሚገኙ ቆንሲላ ጽሕፈት ቤቶች የመገኛ አድራሻ መረጃ በዚህ መመሪያ ጽሑፍ ገጽ 3 ላይ ተሰጥቷል።

የእኔ ልጆች በማደጎ አሳዳጊ ዘንድ ከሆኑ እና እኔ ከአገር እንድባረር ከተደረገ ምን ይፈጠራል?

ምንም እንኳ ካገር ቢባረሩም መልሰው ልጆችዎን መያዝ እንደሚፈልጉ ለእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ፣ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው፣ GAL፣ እና የቤተሰብ ሕግ ፍርድ ቤት ዳኛው መንገርና ምክንያቱን ማብራራት ይኖርብዎታል። ሆኖም ግን አንድ ጊዜ CFSA የቸልተኝነት ክስ ፋይልን ከከፈተ በኋላ፣ ምንም እንኳ እርስዎ ከአገር የተባረሩ ቢሆንም የፍርድ ክርክሩ ይቀጥላል እና የእርስዎ ልጆች የፍርድ ክርክሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከእርስዎ ጋር ለመቀላቀል ወደ የትም ቦታ መጓዝ አይችሉም። እንደ መጨረሻ አማራጭ፣ የቤተሰብ ፍርድ ቤት ዳኛው በእርስዎ አገር ከእርስዎ ጋር እንዲኖሩ መላክ መቻል አለመቻላቸውን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል።

ለቤተሰብ ሕግ ፍርድ ቤት ዳኛው፣ ለጉዳይ ክትትል ሠራተኛው፣ ለGAL፣ እና ለእርስዎ የቤተሰብ ሕግ አማካሪ ጠበቃ እርስዎ ከአገር ሊባረሩ የሚችሉበትን ትክክለኛ ግምታዊ ቀን እና በራስዎ አገር ውስጥ የሚገኙበት አድራሻ ካልዎት ይህንንም ሊሰጡዋቸው ይገባል። በተጨማሪ የእርስዎ ጓደኛ ወይም ዘመድ ልክ እንደ የእርስዎ ማግኛ ነጥብ ሆነው እንዲያገለግሉ የእርስዎን በዩኤስ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ የታመነ ዘመድ ወይም ጓደኛ መገኛ አድራሻን ሊሰጡ ይችላሉ።

የእርስዎ ልጆች ከዩናይትድ ስቴትስ ውጭ እንዲጓዙ ፓስፖርት ሊኖራቸው ይገባል። የርስዎ ልጆች ፓስፖርት ከሌላቸው እና የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ዜጎች ከሆኑ፣ እርስዎ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሌሉ ለእነርሱ ፓስፖርት ማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን አሁኑኑ የእርስዎ ልጆች ፓስፖርት እንዲያገኙ ማገዝ አስፈላጊ ነገር ነው። ሁለቱም ወላጆች ከሕፃኑ ጋር ቅርብ ግንኙነት ካላቸው ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ለሁሉም ሕፃናት ፓስፖርት እንዲሰጥ ሁለቱም ፈቃደኝነታቸውን መግለጽ አለባቸው። ከልጅ የልደት ምስክር ወረቀት እና ከልጁ ጋር ያላቸውን ሕጋዊ ዝምድና የሚያረጋግጥ ሰነድ ጋር ወላጆቹ የማመልከቻ ቅጽ ማስገባት አለባቸው። ይህ ሂደት በአካል ተገኝቶ መከናወን አለበት። ለተጨማሪ መረጃ፣ የዩኤስ አሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን) ማነጋገር አለብዎት።

ወደ ሜክሲኮ ከተባረሩ፣ ቆንሲላው ድንበር ላይ በሚገኝ ቦታ ልጆችዎ እርስዎን እንዲጎበኝዎት ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ይችላሉ። የእርስዎ ልጅ በጉዲፈቻ ክብካቤ ሥር ካለ፣ የጉዳይ ክትትል ሠራተኛው ለእርስዎ ልጆች ጉብኝት እንዲያደርጉ ፈቃድ ማውጣት እና ቆንሲላውን ማነጋገር ይኖርባቸዋል።

አንዳንድ ጊዜ፣ የእርስዎን ልጆች ነገር ሲያስቡ ሐዘን፣ ብቸኝነት ወይም የመደበት ስሜት ሊሰማቸው ይችል ይሆናል። ይህ ጤናማ ስሜት ነው። የሚሰማዎትን ስሜቶች እና ሐሳቦች ይጻፏቸው፣ ሥዕሎችን ይሣሉ፣ መጽሐፍ ያንብቡ፣ አንዳንድ የእጅ ሥራዎችን ይሠሩ፣ ግጥም ይጻፉ፣ ወይም እርስዎ ከእነርሱ ጋር መልሰው በሚገናኙበት ቀን ጥሩ ስሜት እንዲሰማዎት የሚያደርጉዎትን የሆነ ነገር ያድርጉ። እነርሱ ስለ እርስዎ እንዲጨነቁ ሳያደርጉ ደብዳቤ መጻፍ የሚችሉ ከሆነ ለልጆችዎ ደብዳቤ ይጻፉላቸው። ሌላው ሳይቀር እርስዎ ምን እንደሚሰማዎት ለእርስዎ ልጆች ሊጽፉላቸው ሊፈልጉ ይችሉ ይሆናል ሆኖም ግን ደብዳቤውን መልሰው እስኪያገኙዋቸው ድረስ ራስዎ ጋር በጥንቃቄ ያስቀምጡት። ለእርስዎ ልጆች ደህንነት ሲባል፣ ደስተኛ ይምሰሉ፣ ምን ያክል ለእርስዎ ቦታ እንዳላቸው እና ጤናማ እና ደስተኛ መሆን እንዳለባቸው ይንገሩዋቸው።

ለእርስዎ ልጆች ደኅንነት ይታገሉ እና ከእነርሱ ጋር እንደተቀራረቡ ይቆዩ። በጭራሽ ተስፋ አይቁረጡ! የእርስዎ ልጆች እና የእርስዎ ቤተሰብ እርስዎ ተስፋ ባለመቁረጥዎ ይኮሩብዎታል።

 

Back to top